ባሕር ዳርን ለነዋሪዎቿ እና ለጎብኝዎች ምቹ ለማድረግ የሚያሥችል የመሰረተ ልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡

187
ባሕር ዳርን ለነዋሪዎቿ እና ለጎብኝዎች ምቹ ለማድረግ የሚያሥችል የመሰረተ ልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር: የካቲት 22/2013 ዓ.ም (አብመድ) በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በዓለም ባንክ፣ በከተማ አስተዳደሩና በክልሉ መንግሥት 13 ነጥብ 25 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የመንገድ ባለሥልጣን ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ሥራው 35 በመቶ አፈጻጸም ላይ መድረሱንም የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አብቧል ሙላት ተናግረዋል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ የመሠረተ ልማት ችግር በሚታይባቸው ክፍለ ከተሞች የማኅበረሰቡን ጥያቄ መነሻ በማድረግ በዳግማዊ ሚኒልክ እና በአፄ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተሞች የስፖርት ማዘውተሪያ፣ በተለምዶ አሮጌ ዲፖ የአረንጓዴ ልማትና በሁሉም ክፍለ ከተሞች የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡ የሚሠሩ መሠረተ ልማቶች የኅብረተሰቡን ፍላጎት መሠረት ያደረጉና የከተማዋን ውበት ከፍ የሚያደርጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
እንደ ምክትል ሥራ አሰስኪያጁ ገለፃ እየተሠሩ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ሥራዎች የከተማዋን ገጽታ ከፍ ከማድርጋቸው በተጨማሪ ለ49 ድንጋይ ጠራቢ ማኅበራት፣ ለ44 ድንጋይ አንጣፊ ማኅበራትና ለ32 የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን ለሚሠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አስረድተዋል፡፡
ለከተማዋ ውበት ትልቅ አስተዋፅዖ የሚኖረው በ4 ነጥብ 71 ሄክተር መሬት ላይ በ32 ሚሊዮን ብር የአርንጓዴ ልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ምክትል ሥራ አስኪያጁ ነግረውናል፡፡ የጣና ሐይቅ እና የዓባይ ወንዝ ዳርቻዎችን ለዜጎችና ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ የዲዛይን ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በቀበሌ አራት በመሐል ከተማ የገበያ ማዕከላት አካባቢ ለከተማዋ ገጽታ የሚመጥን የመኪና ማቆሚያ፣ ሰው ሠራሽ ፏፏቴ፣ የህፃናት መጨዋቻ እና መሰል አገልግሎቶችን ያሟላ እና በ45 ቀናት ውስጥ የሚጠናቅ የዲዛይን ሥራም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ገንዘብ በማዋጣት ረገድ የጣና ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገባቸውን ምክትል ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡ ኅብረተሰቡ መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ በ70 ቀናት ውስጥ ለማጠናቅ እየተሠራ ነውም ተብሏል፡፡ ኅብረተሰቡ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በንፅህና መያዝ፣ መንከባከብና መጠበቅ እንዳለበት ምክትል ሥራ አስኪያጁ መልዕክት አስተላፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበኩር ጋዜጣ የካቲት 22/2013 ዓ.ም ዕትም
Next articleየሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር 580 በመቶ እድገት ማሳየቱን የኢፌዴሪ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡