
የአዊ ህዝብ የልማት ትብብሩንና ሰላም ወዳድነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።
ባሕር ዳር: የካቲት 20/2013 ዓ.ም (አብመድ)የቲሊሊ ከተማ የከተማ አስተዳደርነት እውቅና መርሐ ግብር ዛሬ ተከናውኗል።። የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የክልልና የብሔረሰብ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባይነሳኝ ዘሪሁን እንዳሉት የቲሊሊ ከተማና አካባቢው በመሰረተ ልማት ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የህዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ነው። ህዝቡ በራሱ አቅም የልማት ክፍተቶችን በመለዬትና ሐብት በማሰባሰብ ትምህርት ቤቶችንና ሌሎችን ማህበራዊ ተቋማትን እየገነቡ መሆኑን አንስተዋል። የክልሉ መንግስትም የብሔረሰብ አስተዳደሩን የመልማት ጥያቄዎች ለመሙላት እያደረገ ያለውን ጥረትንም አመስግነዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር የቲሊሊ ህዝብ የመንግስትን የልማት ትግበራ ክፍተት ለመሙላት እያከናወነ ያለው ተግባር ለሌሎች የክልሉ አካባቢዎች አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል።
የአዊ ህዝብ ልማት ወዳድና ለሰላም መስፈን በቀዳሚነት የሚሰለፍ ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ይህንን ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
የክልሉ መንግስትም የከተሞችን አቅም ለማሻሻልና የህዝቡን የመልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል። ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎቹ በህዝብ ተሳትፎ ከ4 ነጥብ 5ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባ ኪሊ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መርቀዋል።
በህዝብ ተሳትፎ የተገነባውን የቲሊሊ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ክፍልም ጎብኝተዋል።
በከተማው የተገነባውን ዱቄት ፋብሪካንም ተመልክተዋል። በዚህ ዓመት 30 ከተሞች ወደ ከተማ አስተዳደርነት አድገዋል።
ስማቸው እሸቴ -ከቲሊሊ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ