
ወቅቱ ለሚጠይቀው የቴክኖሎጂ ሽግግር ሰልጣኞች በትምህርት ያገኙትን እውቀት ሊጠቀሙ እንደሚገባ የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አሳሰቡ፡፡
ባሕር ዳር: የካቲት 20/2013 ዓ.ም (አብመድ) የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እና የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ባሕር ዳር ሳተላይት ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስለጠኗቸውን ተማሪዎች አስመረቁ፡፡
በ2008 ዓ.ም የቀድሞው የፌዴራል ቴክኒክ እና ሙያ ኢንስቲትዩት የአሁኑ የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ባሕር ዳር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የሳተላይት ካምፓስ በአራት የትምህርት ዘርፎች ተማሪዎችን ተቀብሎ ሲያሰለጥን ቆይቷል፡፡
በመደበኛው እና በተከታታይ የትምህርት ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ እና ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 5 በተለያዩ መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ አስመርቀዋል፡፡
የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ፈለቀ ውቤ በተማሪዎች የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ ‹‹የእንኳን ደስ አላችሁ›› መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ወቅቱ ለሚጠይቀው የቴክኖሎጂ ሽግግር ሰልጣኞች በትምህርት ያገኙትን እውቀት እና ክህሎት ሊጠቀሙ ይገባልም ብለዋል፡፡ ተማሪዎችም በትምህርት ቆይታቸው የንደፈ ሃሳብ እውቀት ብቻ ሳይሆን የተግባር ክህሎት ማግኘታቸው በሥራ ዓለም ለሚገጥሟቸው ፈታኝ ሁኔታዎችም አጋዥ ግብዓት ይሆናል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ካምፓስ 102 ተማሪዎችን በአራት የትምህርት መስክ በመጀመሪያ ዲግሪ አስመርቋል፡፡
የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ 2 ሺህ 278 ሰልጣኞችን ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 5 በ14 የሙያ ዘርፎች አስመርቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ