የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኖርዌይ አቻቸው ጋር ተወያዩ፡፡

260
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኖርዌይ አቻቸው ጋር ተወያዩ፡፡
ባሕር ዳር ፡ የካቲት 19/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢኔ ኤሪክሰን ሰሬይድ ጋር በስልክ ተወያዩ፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን እንዳሉት ማንኛውም የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ ተቋም ወደ ትግራይ ክልል መግባትና የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ማቅረብ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት በእጅጉ እየተሻሻለ መምጣቱን እና መሰረታዊ አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ክፍያም እንዲመቻች እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ምንም እንኳን እስካሁን ድጋፉ ወደ 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ የተደረሰ ቢሆንም መንግሥት 70 በመቶ የሚሆነውን የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶችን በመሸፈን የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡
የኖርዌይ መንግሥትን ጨምሮ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚደረገው ድጋፍም እንደሚበረታታ አስታውቀዋል፡፡ በክልሉ የሰብአዊ መብት ጥሰት ስጋቶችን አስመልክቶ አቶ ደመቀ እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግሥት ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና ከፌዴራል ፖሊስ ሀይል የተውጣጡ ባለሙያዎችን በማሰማራት ምርመራ እያተካሄደ መሆኑን እና ችግሩን ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተሳሳተ መረጃ የቀረቡ ክሶች እና ከአንዳንድ ኢ-ሚዛናዊ የሆኑ የመገናኛ ብዙኃን ዘመቻዎች ቢኖሩም መንግሥት ለሰብአዊ ድጋፍ የበለጠ አመቺ ሁኔታን እየፈጠረ በመሆኑ በክልሉ ማንኛውንም ወንጀል ፈፃሚዎችን ለሕግ ለማቅረብ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አክለዋል፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ስላለው የሦስትዮሽ ድርድር ሁኔታ በተመለከተ አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር በታማኝነት ስትደራደር መቆየቷን ጠቅሰዋል፡፡ ወደፊትም ከኮንጎ መሪዎች ጋር በመሆን ልዩነቶች መሻሻል እንደሚጀምሩ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡
የግድቡ ሙሌት ሊከናወን ከታቀደው መጪው የዝናብ ወቅት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ድርድሩ ስኬታማ እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ በሁለቱ ባለሥልጣናት የጋራ መግባባት ውይይቱ መጠናቀቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው የገለጸው፡፡
በየማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleዝክረ ዓድዋ ዝግጅት የሁሉም አፍሪካውያን መሆን እንዳለበት በዩጋንዳ ማኬሬሬ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁር አስገነዘቡ፡፡
Next article‹‹የአድዋ ድል ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ የይቻላልን ስነ-ልቦና ያጎናጸፈ ነው›› የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባር