ኅብረተሰቡ ለወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ንቁ ተሳትፎና ትብብር በማድረግ ክልሉ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆን የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ ጠየቀ፡፡

623
ኅብረተሰቡ ለወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ንቁ ተሳትፎና ትብብር በማድረግ ክልሉ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆን የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ ጠየቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 18/2013 ዓ.ም (አብመድ) ወሳኝ ኩነት ዜጎች ማንነታቸውን ከማወቅ ጀምሮ በምዝገባው አማካኝነት ተፈላጊ መረጃዎችን በሕጋዊ መንገድ በመያዝ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸውን ቀላል ያደርጋል፤ መንግሥትም ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ በመያዝ የዜጎችን ፍላጎት በመረዳት፣ ፖሊሲ በመቅረጽና በማቀድ፣ ሀገርን በዘመናዊ መንገድ ለማስተዳደር እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያስችለዋል፡፡
የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲም ኅብረተሰቡም ለወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ንቁ ተሳትፎና ትብብር በማድረግ ክልሉ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል፡፡
የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ ከዓለም ባንክና ከፌዴራል ኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ለክብር መዝገብ ሹሞች በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባና ተያያዥ ሥራዎች ላይ በደብረ ታቦር ከተማ የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
እንደ ኤጀንሲው መረጃ በኢትዮጵያ ወሳኝ ኩነት መመዝገብ የተጀመረው ከሐምሌ 30/2008 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወሳኝ ኩነት ተብለው ከተያዙት 10 የሰው ልጅ የህይወት ኩነቶች ውስጥ ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ሰባቱን (ልደትን፣ ሞትን፣ ጋብቻን፣ ፍቺን፣ ጉዲፈቻን፣ አባትነትን በራስ ፍላጎት ማወቅንና አባትነትን በፍርድ ቤት ማወቅን) የመመዝገብ ሥራ እያከናወነች ትገኛለች፡፡
የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር አቶ በተግባር እንየው በክልሉ በ3 ሺህ 973 ቀበሌዎች ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንደጠቀሱት ኅብረተሰቡ ጠቀሜታውን ተረድቶ በወሳኝ ኩነቶች ላይ በወቅቱ አለማስመዝገብ ችግር እየተስተዋለ ነው፤ የሥራ ኀላፊዎችም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ለኅብረተሰቡን ግንዛቤ እየፈጠሩ አይደለም፤ የወሳኝ ኩነቶች መዝጋቢ አካላት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርና የበጀት እጥረት ተግዳሮቶች አሉበት፡፡ የስልጠናው ዓላማ በክልሉ ውስጥ ባሉ ቀበሌዎች አዲስ ለተቀጠሩ የክብር መዝገብ ሹሞች በምዝገባ አፈጻጸም ላይ ያጋጠሙ የሽፋን እና የጥራት ችግሮችን ለመፍታት እንደሆነ ነው አቶ በተግባር የገለጹት፡፡ የሰልጣኞችን አስተሳሰብ እንደሚያሻሽልም ጠቁመዋል፡፡
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀለመወርቅ ምህረቴ ትክክለኛ ባልሆነና ባግባቡ ባልተደራጀ መረጃ የክልሉ ሕዝብ እንዳይጎዳ የወሳኝ ኩነትን መረጃ በትክክል መዝግቦ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ይህ ከክብር መዝገብ ሹሞች የሚጠበቅ ኀላፊነት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ በሚጠናቀረው መረጃ በክልሉ የሚታየውን ልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት የክብር መዝገብ ሹሞች የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ – ከደብረታቦር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ከቀደሙት የቀደመ ርቆ ለመሄድ ያለመ”
Next article“ሱዳን በጉልበት የያዘችውን ቦታ ለቅቃ እንድትወጣ የኢትዮጵያ መንግሥት የጊዜ ገደብ ሊኖረው ይገባል” የታሪክ ምሁር