በግማሽ ዓመቱ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ 208 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደሥራ መግባታቸውን የሱማሌ ክልል አስታወቀ፡፡

121
በግማሽ ዓመቱ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ 208 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደሥራ መግባታቸውን የሱማሌ ክልል አስታወቀ፡፡
የዘርፉን ማነቆ ለመፍታትም ከ1 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር በላይ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 17/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሱማሌ ክልል ሸበሌን የመሰሉ ወንዞች፣ እምቅ የሆነ ማዕድን፣ የእንስሳት ሃብት፣ ለግብርና ምቹ የሆነ ሰፊና ያልተነካ የእርሻ መሬትን የታደለ ነው፡፡ ለቱሪዝም መዳረሻ የሚሆን በርካታ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ሃብቶችን የታደለው ክልሉ እስካሁን ለሀገር በሚጠቅም መልኩ ሥራ ላይ ግን አልዋለም፡፡
ለዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየው ፍትሐዊነት የጎደለው አስተዳደር ክልሉ ሃብቱን እንዳይጠቀም አድርጎት ቆይቷል ያሉት የሱማሌ ክልል የኢንቨስትመንትና ዳያስፖራ ቢሮ ኀላፊ አቶ አብዱሰላም የሱፍ ናቸው፡፡
ክልሉ ገብቶበት ከነበረው ቁልቁለት በማውጣት እና የክልሉ ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ ለማድረግ አዲሱ የለውጥ አመራር የሠራው ሥራ ውጤት ማስመዝገቡን ከአብመድ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ አብዱሰላም ገለፃ በ2013 ዓ.ም የመጀመሪያው 6 ወር ብቻ 208 ባለሀብቶች በክልሉ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደሥራ ገብተዋል፡፡ ክልሉ እንደ ሀገር የነበረበትን የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ውስንነት እና የአሠራር ማነቆዎችን ለመፍታት በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን ያወሱት አቶ አብዱሰላም በርእሰ መሥተዳድሩ የሚመራ የሱማሌ ክልል የኢንቨስትመንት ቦርድ ተዋቅሮ በየ3 ወሩ እየገመገመ መፍትሄ ይሰጣል ብለዋል፡፡
የሱማሌ ክልል የሚታወቅበት ሰፊ የእንስሳት ሃብት ቢኖረውም ባለቤቱ የሱማሌ ሕዝብ አልነበረም፤ ህገ ወጦችን ድንበር በማሻገር ሲበለፅጉበት ቆይተዋል ያሉት አቶ አብዱሰላም አሁን አሠራሩን ሕጋዊ መልክ በማስያዝ የሕዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በቀን ከ16 ሺህ ሊትር በላይ ወተት የሚያቀነባብር ፋብሪካ በቅርቡ ሥራ ይጀምራልም ተብሏል፡፡
የክልሉን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ የመንገድ መሰረተ ልማት ሥራ ላይ በትኩረት እየተሠራ ነውም ተብሏል፡፡ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በክልሉ ውስጥ ከ1 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር በላይ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፤ ይህም በዘርፉ የሚስተዋለውን ማነቆ የሚፈታ ይናል ብለዋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የኢንቨስትመንት ፋላጎት የክልሉን ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ከማነቃቃቱም በተጨማሪ ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን አቶ አብዱሰላም ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም በክልሉ ሰፊ የእንስሳት ሃብት በመኖሩ በስጋ እና በወተት ልማት ዘርፍ ባለሀብቶች ወደክልሉ ቢገቡ ውጤታማ ይሆናሉ ተብሏል፡፡ በእርሻ ዘርፍም ክልሉ ገና ያልተነካ እምቅ ሃብት ስላለው ባለሃብቶች ገብተው እንዲያለሙ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“በትግራይ ክልል 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ተጠቃሚ ሆነዋል” ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት
Next article“የፌዴራል ምንግሥትን አሳምነን ያመጣናቸዉን የልማት ፕሮጀክቶች መሪዎችና የልማቱ ተጠቃሚዎች ተመልሰን የልማቱ ችግር መሆን የለብንም” የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ