
“ለዓመታት የሲዳማ ሕዝብ የክልልነት ጥያቄ ለመለሱት የለውጡ መሪዎች ምስጋና ይገባቸዋል” የሲዳማ ክልል ርእስ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ
ባሕር ዳር፡ የካቲት 15/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሲዳማ ክልል የመንግሥት ምሥረታ ሥነ ሥርዓት በሐዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡ በመንግሥት ምሥረታው ሥነ ሥርዓት ንግግር ያደረጉት የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ ለዘመናት የቆዬው የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄ መልስ በማግኜቱ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
የሲዳማ ሕዝብ በክልል እንዲደራጅና በሀገሪቱ እኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ያደረገው መራራ ትግል ፍሬ አፍርቷል ነው ያሉት፡፡
የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄ ፍትሐዊ ጥያቄ በመሆኑ በምንም መመዘኛ የሚነፈገው አልነበረም፤ ነገር ግን ጥያቄውን ያነሳው ሕዝብ ባለፈው ሥርዓት ግፍ ሲደርስበት ቆይቷል ብለዋል፡፡ ያለፈው ጨካኝ ሥርዓት የሕዝብን ጥያቄ ለማዳፈን ግፍ መፈፀሙንም ተናግረዋል፡፡
ይህም ሆኖ የሲዳማ ሕዝብ ለነጻነት፣ ለእኩልነት፣ ለክብርና ለጥቅሙ ከመታገል ወደኋላ ያለበት ወቅት አልነበረም ብለዋል፡፡ ትግሉ በትውልድ ቅብብሎሽ የመጣ መሆኑን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ የመጣው ለውጥና የለውጡ መሪዎች ጥያቄው ሕገ መንግሥታዊ ምላሽ እንደሚሰጠው በማመን በሕጋዊ መንገድ መልሷል ነው ያሉት፡፡
የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ እየተከተልን ያለነውን ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ይበልጥ እየዳበረ፣ ሕዝቦችም በመቻቻልና በሕብረት የበለፀገች ሀገር ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የሲዳማን የሕዝብ ጥያቄ በመመለስ እውነተኛ ፌደራሊዝም እንዲተገበር ላደረጉት የለውጡ መሪ ለጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና ሌሎች መሪዎች ምስጋና ቅርበዋል፡፡
የሲዳማ ሕዝብ አቃፊ፣ ሰው አክባሪ፣ እንግዳ ተቀባይ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ክልሉ በተመሰረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፍፁም ሰላማዊ በመሆን ለልማት ምቹ ሆኗልም ብለዋል፡፡
ክልሉ በልማት ለሚሠማሩ ባለሀብቶች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የሲዳማ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ሀገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
