
በጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የተመራ የመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጉብኝት እያደረገ ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 15/2013 ዓ.ም (አብመድ) ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ከልዑል ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን፣ የአቡዳቢ አልጋ ወራሽ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ጋር ተገናኝተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተላከ መልዕክት አድርሰዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ያለው ግንኙነት በሁሉም ዘርፍ እየተጠናከረ እንደመምጣቱ መጠን በሁለቱ ሀገራት የመከላከያ ተቋማት ያለው ግንኙነት በዚያው ልክ እየተጠናከረ፣ የትብብር አድማሱም እየሰፋ መሄዱን ጠቅሰዋል፡፡
ልዑል ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያንም በበኩላቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተላከውን መልዕክት ከተቀበሉ በኋላ የሀገራቱ ግንኙነት ህዝቦችን ተጠቃሚ ስለሚያደርግ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ እንዲሄድ ቁርጠኛ አቋም እንዳላት ተናግረዋል።
የሀገራቱ ግንኙነት በኢኮኖሚ፣ በትምህርትና ቴክኖሎጂ፣ በደኅንነትና ጸጥታ ዘርፍ እንዲሁም በወታደራዊ ግንኙነቶች ይበልጥ እንዲጠናከር በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በኩል ያለውን ቁርጠኝነት በመጥቀስ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡
ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ከልዑል አልጋ ወራሽ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር በምስራቅ አፍሪካ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታና የትግራይ ክልል ስለተካሄደው የሕግ ማስከበር ወታደራዊ እርምጃና አሁን ስለሚገኝበት ሁኔታም አብራርተውላቸዋል፡፡
ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ በመጭዎቹ ቀናቶች ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የመከላከያ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጋር እንደሚመክሩ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘ መረጃ ያመለክታል ።
