በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዳሳሰባቸው የከተማዋ የምክር ቤት አባላት ተናገሩ።

300
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዳሳሰባቸው የከተማዋ የምክር ቤት አባላት ተናገሩ።
ባሕር ዳር ፡ የካቲት 13/2013 ዓ.ም (አብመድ) በባሕር ዳር ከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራን በአብቁተ የተቀማጭ ገንዘብ ማሳደግ እንደሚገባ የከተማዋ የሥራ ዕድል ፈጠራ አፈፃጸም በምክር ቤት ደረጃ በተገመገመበት ወቅት ተገልጿል፡፡ የሥራ አጥነት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንና የሥራ ዕድል ፈጠራ አፈፃጸሙ ውስንነት እንዳለበት የከተማዋ የምክር ቤት አባላት አንስተዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ለመተግበር ከታሰበው የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ አፈፃጸሙ 37 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ መሆኑንም የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል፡፡ በሥራ ዕድል ፈጠራ 80 በመቶው ቋሚ እንዲሆን ቢጠበቅም በስድስት ወራቱ ከተፈጠረላቸው መካከል 46 ነጥብ 5 በመቶው የሚሆኑት ጊዜያዊ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ናቸው፡፡
የሴቶች ድርሻ 50 በመቶ መሆን ሲገባው 39 በመቶ ብቻ መሆኑም አባላቱን አሳስቧቸዋል፡፡
የተዘዋዋሪ ብድር አሰጣጥ መመሪያ አስቸጋሪ መሆን፣ የመሬት አቅርቦትና አዳዲስ ሼድ አለመገንባት በወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ የተስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን አንስተዋል። ችግሩ ተባብሶ እንዳይቀጥል ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ኀላፊ አስሜ ብርሌ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ሠፊ ክፍተት መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በጀት ባለመያዙ አዲስ ሼድ እንዳልተገነባ ተናግረዋል፡፡
የተዘዋዋሪ ፈንድ የብርድ አመላለስ መመሪያው አበዳሪ ተቋም ያስቀመጠው መሥፈርት በመሆኑ ከተወሰደ ብድር መካከል 97 በመቶ ያህሉ ካልተመለሰ መበደር እንደማይቻል አስገንዝበዋል፡፡ መምሪያ ኀላፊው 13 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ገደማ ያልተመለሰ እዳ መኖሩን ተናግረዋል፡፡ እዳው ሳይመለስ ተጨማሪ የብድር ጥያቄ ማቅረብ እንደማይቻልም ገልጸዋል፡፡
ችግሩን ለመቀልበስ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ መሥራት እንደሚገባ የመምሪያው ኀላፊ ተናግረዋል፡፡ የሥራ አጥነት ምጣኔው ለማከናወን ከታቀደው የላቀ መሆኑን አንስተዋል:: ከዕቅድ በላይ መሥራት ካልተቻለ በቀጣይ አስቸጋሪ እንደሚሆንም ነው የገለጹት፡፡
መደበኛ የብድር አገልግሎት ግን መቀጠሉን በመግለጽ የመሬት አቅርቦት እንዲኖር እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። የመሰረተ ልማት በጀት መያዙንም አስታውቀዋል፡፡
“ለሥራ ዕድል ፈጠራ ብድር የሚያቀርበው አብቁተ ነው፤ የከተማዋ ነዋሪዎች ግን ተቋሙን እየተጠቀሙ አይደለም” ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከ500 በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የቦታ አቅርቦት ችግር ገጥሟቸዋል፡፡
Next articleለዓመታት የጨለመች በወራት አበራች።