
የባሕር ዳር ከተማ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ጥያቄ በአፋጣኝ ሊፈታ እንደሚገባ የምክር ቤት አባላት አሳሰቡ፡፡
ባሕር ዳር ፡ የካቲት 12/2013 ዓ.ም (አብመድ)
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር ስምንተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳኅሉ በግማሽ በጀት ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራትን ሪፖርት ለምክር ቤት አባላት አቅርበዋል።
የምክር ቤት አባላቱም በቀረበው ሪፖርት ላይ ሀሳብ፣ አስተያዬት እና ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የመኖሪያ ቤት ችግር በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ከሚነሱ ቁልፍ ችግሮች መካከል ቀዳሚ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ የክራይ ቤት ዋጋ ንረት መኖሩንም አንስተዋል፡፡
ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ለተደራጁ የከተማዋ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ለመስጠት በተደጋጋሚ ቃል ሲገባ እንደነበርም ነው የምክር ቤት አባላቱ የተናገሩት፡፡ 601 ማኅበራት ቦታ እንዲያገኙ በምክር ቤት ተወስኖ እንደነበር የምክር ቤት አባላቱ አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ተግባር መቀየር እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡ መጠለያ ማግኘት ከመሠረታዊ ፍላጎቶች መካከል ቀዳሚ መሆኑን በማንሳትም ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሥራ አስኪያጅ ሙሉዓለም ተፈራ በተነሱት ሀሳቦች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ቀደም ብሎ በከተማዋ ከ27 ሺህ ያላነሰ አባላት ላላቸው 589 ማኅበራት በአንድ ጊዜ እውቅና መሰጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህም በተዘጋጀ ቦታና በተደራጀው የሰው ቁጥር መካከል አለመመጣጠን መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ በዚህም 13 ሺህ አባላት ብቻ ቦታ መውሰዳቸውን አስገንዝበዋል፡፡
ከዚያ ወዲህ የባሕር ዳር ከተማ መዋቅራዊ ፕላን ተሠርቶ አለመጠናቀቅ በችግር አንስተዋል፡፡ ለማኅበራት ቤት መሥሪያ 100 ካሬ እንዲሰጥ ከተወሰነ በኋላ ወደ 150 ማደጉ እና የካሳ አዋጅ መሻሻልም በሚፈለገው ደረጃ ማስተናገድ እንዳይቻል ያጋጠሙ ችግሮች ናቸው፡፡ በቅርቡ ግን ችግሮቹን በመፍታት ቦታ የመለየት ሥራ መሠራቱን ጠቅሰዋል፡፡ በተያዘው ዓመት ማኅበራትን ለማስተናገድ ቁርጠኝነት መኖሩንም አስታውቀዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ (ዶክተር) የቤት ማኅበር ጉዳይ በርካታ ሰዎች በትኩረት የሚከታተሉት መሆኑን አንስተዋል፡፡ ለዓመታት ሲንከባለል የቆዬ በመሆኑ በከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን አስገንዝበዋል፡፡ ቅድሚያ ተሰጥተው ሊሠሩ ከታቀዱ ፕሮጀክቶች መካከል የመኖሪያ ቤት ጉዳይ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፤ ችግሩን በጥንቃቄ መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ዘንዘልማ እና ዲያስፖራ ሰፈሮች 541 ማኅበራትን ማስተናገድ የሚችል ቦታ ተገኝቷል፤ መሸንቲም 25 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል፡፡ ነገር ግን በማኅበራት መካከል ግጭት እንዳይፈጠር ሕጋዊ እውቅና ተሰጥቷቸው ገንዘብ የቆጠቡ ማኅበራትን በአንድ ጊዜ የማስተናገድ ዕቅድ እንዳለ አመላክተዋል፡፡ 601 ማኅበራትን የሚያስተናግድ ቦታ የማፈላለግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የከተማዋን መዋቅራዊ ፕላን በፍጥነት በማስተካከል የኤሌክትሪክ ማስፋፈያ እና የኢንቨስትመንት እንዲሁም ተያያዥ ቦታዎችን ታሳቢ ያደረገ ልማት ይሠራልም ብለዋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ችግር በሚፈታ ጊዜ አርሶ አደሮች እንዳይጎዱም ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ለዚህም የምክር ቤቱ ርዳታ እና የክልሉ መንግሥት ጣልቃ ገብነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
