
የካቲት 12 የሰማእታት ቀን
ባሕር ዳር ፡ የካቲት 12/2013 ዓ.ም (አብመድ)
ጣሊያን በ1879 ዓ.ም ዶጋሌ ላይ፣ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ደግሞ የካቲት 23/1888 አድዋ ላይ ሽንፈትን ተከናንባለች። በተለይም ደግሞ የጣሊያን አድዋ ላይ መሸነፍ ያበሳጫቸው አውሮፖውያን ኢትዮጵያን ለመበቀል የተለያዩ ሴራዎችን ሠርተዋል፡፡ ከእነዚህ ሴራዎች ውስጥ በ1898 ዓ.ም እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ጣሊያን ለንደን ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ስር እንድተዳደር መወሰናቸው አንዱ ነበር።
በ1928 ዓ.ም በእዚያ ዘመን በተፈፀሙት የወረራ ታሪኮች ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጣልያን ግዙፍ ኀይሏን አሰልፋ ኢትዮጵያን ድጋሜ ወረረች። ከመሬት በታንክ፣ በመድፍና በመትረየስ፣ ከአየር ቦምብ በሚጥሉ እና የመርዝ ጋዝ በሚያዘንቡ አውሮፕላኖች የኢትዮጵያን ሕዝብ ጨፈጨፉ፡፡
የኢትዮጵያ ጦር ሀገሩን ላለማስደፈር ጠላትን በሰይፍና በጎራዴ ጭምር ተፋለመ። ነገር ግን የጣሊያን ጦር የመሣሪያ የበላይነት ሚያዝያ 27/1928 ዓ.ም አዲስ አበባ ድረስ እንዲዘልቅ ረዳው። ጣሊያን አዲስ አበባ ድረስ መዝለቅ ቢችልም ኢትዮጵያውያን ግን በጠላት ጦር ላይ ጥቃት መሰንዘርን አላቆሙም ነበር። በዱር በገደሉ እና በዋና ዋና ከተሞች ከፈጸሟቸው ጥቃቶች መካከል አንዱ በግራዚያኒ ላይ የተደረገው የግድያ ሙከራ ነበር፡፡
ግራዚያኒ የካቲት 12/1929 ዓ.ም ስለጣሊያን ንጉሥ ቪክቶር ኢማኑኤል ልጅ መውለድ ደስታ ለማብሰር በገነት ልዑል ቤተ መንግሥት አዳራሽ ሹማምንቱንና ሕዝቡን ሰበሰበ፡፡ በዝግጅቱ አብርሃም ደቦጭ፣ ሞገስ አስግዶም፣ ስምኦን አደፍርስ፣ ስብሃት ጥሩነህ እና ሌሎች ወጣቶች ቦንብ ይዘው ወደ ስብሰባው ገቡ፡፡ በተለይ አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስግዶም በኤርትራ በነበሩበት ወቅት የጣሊያን መንግሥት በኤርትራ ሕዝብ ላይ ይፈጽም የነበረውን ግፍ ያውቁ ሥለነበር ከፍተኛ ቁጭት ነበረባቸው፡፡
ወጣቶቹ ወደ አዳራሹ እንደገቡ ግራዚያኒ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ስለ አርበኞች እና ስለ ንጉሡ በንቀት ይናገር ነበር፡፡ ወጣቶቹ በግራዚያኒ የንቀት ንግግር እና በስብሰባው ውስጥ በታደመው ተሰብሳቢ ተናደዱ፤ ወደ ግራዚያኒ ቀስ ብለው በመጠጋት ሰባት ቦንቦችን በተከታታይ ወረወሩ፡፡ ተሰብሳቢው የመጀመሪያው ቦንብ ፍንዳታ የደስታ ርችት መስሎት ስለነበር አልተደናገጠም፡፡ በሁለተኛው የቦንብ ፍንዳታ ግራዚያኒ ተመትቶ ከብዙ ቦታ ላይ ቆሰለ፤ የጦር ኃይል አዛዥ የነበረውን አውራሊያ ሊአታ አይኑ ጠፋ፤ እግሩ ተቆረጠ፡፡ ሌሎች ሹማምንትም ሕይወታቸው አለፈ።
ወጣቶቹ ቦንቡን ወርውረው እና አዳራሹን አተራምሰው እንደወጡ በጓደኛቸው በስምኦን መኪና ከአዲስ አበባ ወደ ፍቼ በማቅናት ከአርበኞች ጋር ተቀላቀሉ። እስከ 1932 ዓ.ም ድረስም ጠላትን ተዋጉ። በመጨረሻም በጠላት ጦር ቋራ ላይ ተይዘው ተገደሉ።
የግፈኛው ንጉሥ ኡምቤርቶ ጦር ማጭድ፣ ጎራዴ፣ ጦርና ጋሻ የያዘውን የኢትዮጵያ ጦር በመድፍና በዘመኑ መሳሪያዎች ጨፍጫፏል፡፡
ከ41 ዓመታት በኋላ ተመልሶ ለወረራ የመጣው በማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ የሚመራው የፋሺስት ጦር ከየካቲት 12 እስከ የካቲት 14 ድረስ ባሉት ሦስት ቀናት ከ30 ሺህ በላይ ሠላማዊ ኢትዮጵያውያንን ጨፍጭፏል፡፡ በጭፍጨፋው ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎችን ለመዘከር የካቲት 12 በብሔራዊ ደረጃ እንዲዘከር በ1934 ዓ.ም ታወጀ፡፡
በ1951 ዓ.ም ደግሞ 6 ኪሎ አካባቢ የሚገኘው እና 28 ሜትር ርዝመት እንዳለው የሚነገረው የሠማዕታት መታሰቢያ ሐውልት እንዲቆም ተደርጓል፡፡
የታደሰ በቀለ ዳኘ “ከቀዳማዊ እስከ ቀዳማዊ” እና የጳውሎስ ኞኞ “ኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት” የተሰኙ መጽሐፍትን በማጣቀሻነት ተጠቅመናል፡፡
በዳግማዊ የሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
