
“የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና፣ የምርምር ተቋማት እና የኢንዱስትሪ ትስስር ለሀገር ብልጽግና ቁልፍ ሚና አለው” የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል
ባሕር ዳር፡ የካቲት 11/2013 ዓ.ም (አብመድ) የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና የምርምር ተቋማት እና የኢንዱስትሪ ትስስር የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ሀገሪቱ ያላትን ሃብትና እውቀት ማስተሳሰር የልማትና ብልጽግና ጉዞን ለማሳካት ሰፊ ዕድል ያለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ተፈጻሚነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
ሚኒስትሩ በሳይንስ፣በፈጠራ እና በምርምር ሥራዎች የኢንዱስትሪው ፍላጎትን ያሟላ፣ ምቹ ፣በቂ እና በሚፈለገው ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይልና ግብዓት ለማቅረብ እንዲቻል የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና፣ምርምር፣የፈጠራና ቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግር ጥራትና አግባብነትን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል “የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና፣ የምርምር ተቋማት እና የኢንዱስትሪ ትስስር ለሀገር ብልጽግና ጉዙን ለማሳካት የሚኖረው ሚና ቁልፍ ሚና አለው” ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ በዘርፉ ያሉ ውስንነቶች በመቅረፍ፣የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር እንዲሁም የምርምር ስርፀትን በማጠናከር እና ተግባር ላይ በማዋል ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ነው የተናገሩት፡፡
ከግሉ ዘርፍ ለተሳታፊዎች ልምዳቸውን ያካፈሉት የበላይነህ ክንዴ ቢዝነስ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ በላይነህ ክንዴ ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣትና እድገትና ብልጽግና ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ ከዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከምርምር ተቋማት ጋር ትስስርና ትብብርን በማጠናከር የሀገር ውሰጥ አቅምና እውቀትን ማሳደግ የግድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የተለያዩ የግልና የመንግሥት ተቋማት ልምዳቸውን ማካፈላቸውን ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
