ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 17/2011 ዓ.ም (አብመድ) ትውልዱ ባሕላዊ ቅርሱን ሊጠብቅ እንደሚገባው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሐንስ ቧያለው አሳስበዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ በላልይበላ የአሸንድየ የልጃገረዶች ጨዋታ በዓል አከባበር ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ‹‹ላልይበላ የታሪክ ባለቤት፣ የአማራ ክልል፣ የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ብሎም የዓለም ቅርስ መገኛ ነው›› ብለዋል፡፡ ቀደምት የላልይበላ እናት እና አባቶች ለዓለም ሕዝብ ትልቅ የኪነ ህንጻ ጥበብን እና እውቀትን አበርክተዋል ነው ያሉት አቶ ዮሐንስ፡፡ ባሕላዊ እሴቶችን ለብዙ ሽህ ዓመታት ጠብቀው ለትውልድ ማስተላለፋቸውንም አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ አርበኞች በዓድዋ ላይ ተዋድቀው ኢትዮጵያን ከወራሪዎች ነጻ ባያወጧት ኖሮ አሸንድዬን ጨምሮ ሌሎች ባህላዊና ኃይማኖታዊ በዓላት አይከበሩም ነበር ያሉት አቶ ዮሐንስ ባሕል እና ቋንቋዎችም በመጤ ባሕል እና ቋንቋ ተበርዘው ይጠፉ እንደነበር አመላክተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም አባቶች ለዘመናት ጠብቀው ለትውልዱ ያስረከቡትን ባሕል በመበረዝ የራሳቸውን ማንነት ለመጫን የሚሞክሩ አካላት መኖራቸውን ነው ያስገነዘቡት፡፡

ላልይበላን ጨምሮ መላው ወሎ የአማራ ክልል ማዕከል መሆኑን የዘነጉ ነገር ግን የማይሳካላቸው አካላት መኖራቸውን ያመላከቱት አቶ ዮሐንስ ትውልዱ ሳይከለስ ከአያት ቅድመ አያቶቹ የተረከበውን ባሕሉን ሳይበርዝ ማቆየት እና የራሱን የታሪክ አሻራ ማሳረፍ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ መጭው ዘመንም ለቀጣይ ትውልድ ያማረ እንዲሆን መስራት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡

አማራ ክልል በሰላም፣ በልማት እና በዴሞክራሲ ጎዳና እንዲጓዝ ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልግ የተናገሩት አቶ ዮሐንስ በተለይ ወጣቶች ለአካባቢያቸው እና ለክልላቸው ልማት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፤ የክልሉ መንግስትም ድርሻውን እንደሚወጣ አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ

Previous article“ሰሚ ያጣ ሮሮ” የባሕር ዳር ትራንስፖርት ጽ/ቤት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር.
Next articleእስራኤል በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ እና በጸጥታ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትሰራ ቤንያሚን ኔታንያሁ ተናገሩ፡፡