“እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ፣ በምቀኝነት እርስ በራሳችሁ ተዋግታችሁ ታላለቃችሁ በቀር ሀገራችንን ለሌላ ለባዕድ አትሰጧትም” አጤ ምኒልክ

321
“እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ፣ በምቀኝነት እርስ በራሳችሁ ተዋግታችሁ ታላለቃችሁ በቀር ሀገራችንን ለሌላ ለባዕድ አትሰጧትም” አጤ ምኒልክ
ባሕር ዳር፡ የካቲት 10/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአጤ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ከሚታወቅባቸው የሀገረ መንግሥት ባሕሪያት መካከል ሀገራዊ አንድነትና ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ስትራቴጂ ይጠቀሳሉ፡፡ ጥሩ የሀገር ውስጥ ግንኙነት እና የተሳካ የውጪ ዲፕሎማሲ መፈጠሩም ትልቅ ትሩፋት ተገኝቶበታል፡፡
ንጉሠ ነገሥት አጤ ምኒልክ ገና በጠዋቱ ከዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ጋር በነበራቸው ግንኙነት ለቀጣይ ሕይወታቸው ትምሕርት የወሰዱበትና የጠንካራ መንግሥት መሠረት ያገኙበት ነው፡፡ ስልጣነ መንበሩን በተረከቡበት ጊዜም ከተፎካካሪዎቻቸውና በዙሪያቸው ከነበሩ ሰዎች ጋር ጥብቅ ግንኙነት መፍጠራቸው ወደ ታላቅነት አምርቷቸዋል፡፡
ከአብመድ ጋር ቆይታ ያደረጉት የደብርብርሃን ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የቅርስ አስተዳደር ትምሕርት ክፍል መምህር የሺዋስ እስከዚያው በዘመኑ መልካም የሀገር ውስጥ ግንኙነት እና የተሳካ የውጪ ዲፕሎማሲ መፈጠሩ የኢትዮጵያን ክብር ይበልጥ ከፍ እንዳደረገ አብራርተዋል፡፡
የንጉሡ የውስጥ ግንኙነት መርሕ ከመፎካከር ይልቅ በመተጋገዝ፣ ከመለያዬት ይልቅ ይበልጥ ተቀራርቦ ለታላቋ ኢትዮጵያ ከፍታ በጋራ በመሥራ ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ መምህሩ እንዳሉት ነገሮችን የመቀበል ችሎታና ትሕትናቸው በባላባቶች ዘንድ እምነት እንዲጣልባቸው አድርጓል፡፡ ራስ ሚካኤልና አባ ጅፋር ስልጣን ሲይዙ ግብር እንዲያስገቡ ከማድረግ ባለፈ በሃይማኖታቸውም ሆነ በሌላ ስብዕናቸው ላይ ተጽዕኖ አለማሳደራቸውን በማሳያነት አንስተዋል፡፡ በተመሳሳይ ከንጉስ ተክለሃይማኖት እና ከንጉስ ሚካኤል ጋር በተፎካካሪነት የተጀመረውን ግንኙነት በወዳጅነት በመቋጨት ሁነኛ የፖለቲካ አጋር አፍርተዋል፡፡ ከአባ ጅፋር፣ ከጣይቱ ብጡል ቤተሰቦች፣ ከጎጃም፣ ከየጁ፣ ከበጌ ምድር፣ ከወሎ እንዲሁም ከሸዋ አካባቢ በተለይም ከሜጫና ከቱለማ ኦሮሞ ባላባቶች ጋር ቅርብ ግንኙነት በመፍጠር የጋራ ዓላማ ይዘዋል፡፡ ይህም በንግሥና ዘመናቸው ትልቅ ፖለቲካዊ ድልን እንዲቀዳጁ አስችሏቸዋል፡፡ መላው ኢትዮጵያውያንም በንጉሡ ላይ እምነት እንዲያሳድሩ አድርጓቸዋል፡፡
አጤ ምኒልክ በውጪ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውም የታወቁ መሪ ናቸው፡፡ ከመቅደላ አምልጠው ወደ ሸዋ ካቀኑ በኋላ የውጪ ግንኙነታቸውን ማጠናከር ለንግሥና ዘመናቸው ወሳኝ እንደሚሆን በሚገባ ተረድተው ነበር፡፡ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በመፍጠርም ብዙ አትርፈዋል፡፡ ንጉሠ ነገስቱ ከብዙ መንግሥታት ጋር ግንኙነት ቢፈጥሩም ወሳኝ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የነበራቸው ከጣልያን፣ ከፈረንሳይ እና ከሩሲያ ጋር እንደነበር አቶ የሺዋስ ተናግረዋል፡፡
ከጣልያን ጋር የነበረው ግንኙነት በወዳጅነት ተጀምሮ በደም መፋሰስ የተቋጨ ነው፡፡ ሁለቱ ሀገራት ከ1870ዎቹ መጨረሻ ጀምረው የንግድ እና የወዳጅነት ግንኙነት ፈጥረዋል፡፡ በግንኙነታቸውም ኢትዮጵያ ከጣልያን የጦር መሳሪያ እስከማግኘት ችላ እንደነበር መምህሩ አስታውሰዋል፡፡
“የውጫሌ ስምምነት በአፍሪካ ውስጥ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሉዓላዊ ሀገር ከአውሮፓ ታላላቅ መንግሥታት ጋር ትልቅ ሕጋዊ ስምምነት የተዋዋለችበት፣ ስሟን ከፍ ያደረገ፣ ዝናዋንም ያገነነ ስምምነት ነው” በማለትም ከግንኙነታቸው ሁሉ የኢትዮጵያን ዓለማቀፍ ታዋቂነት ያጎላው የውጫሌ ስምምነት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጣልያን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ሥር ለማድረግ በነበራት ከንቱ ፍላጎት ምክንያት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የዓለምን ታሪክ በቀየረ መልኩ በጦርነት ተቋጭቷል፡፡
ንጉሡ የውጫሌ ውል ትርጉም የተሳሳተ መሆኑን ከተረዱ በኋላ በሀገር ውስጥም በዓለማቀፍ ደረጃም የተለየ ዝግጅት አድርገዋል፡፡ የጣሊያን ተስፋፊዎች የኢትዮጵያን ውስጣዊ ሁኔታ በሚገባ ካለማወቃቸው የተነሳ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር 20 ሺህ ወታደር ብቻ እንደሚበቃ ወስነው ነበር፡፡ ነገር ግን የሀገሪቱ ማዕከላዊ ሥልጣን ይበልጥ መጠናከር፣ ጥቃት በሚፈጽሙ የውጭ ኃይሎች ላይ ያላቸው ጥላቻ መጨመር እና ውስጣዊ ቅራኔዎች መፈታት ኢትዮጵያን አሸናፊ አድርጓታል፡፡
የአጤ ምኒልክ ገና የሸዋ ንጉሥ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ በላቀ የፖለቲካ ብስለታቸውና አርቆ አስተዋይነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ጠንካራ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መዋቅር መዘርጋታቸውም በስፋት ይነገራል፡፡ በጣልያን ጦር ላይ የበላይነትን በማቀዳጀት የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የጭቆና ቀንበር እንዲወገድ መሠረት ጥለዋል፡፡
አጤ ምኒልክ ከጦርነቱ አስቀድሞ ከጣልያን ጋር የነበራቸው ግንኙነት እየተበላሸ መሆኑን ከተረዱ በኋላ ፊታቸውን ወደ ሌሎች ሀገራት አዙረዋል፡፡ እነ ራስ መኮንን እና ዮሴፍ ንጉሴን ጨምሮ ዲፕሎማቶች ወደ ሩሲያ፣ ግሪክ፣ ጣልን፣ ፈረንሳይና ሌሎችም ሀገራት ሄደው የኢትዮጵያን አቋም እንዲያንጸባርቁ አድርገዋል፡፡ ይሕ የዲፕሎማሲ እይታቸው የንጉሡን ደረጃ ይበልጥ ያሳደገ፣ የኢትዮጵያን ክብርና ዝናም ከፍ ያደረገ እንደነበር ነው የታሪክ ምሁሩ የተናገሩት፡፡ በተለይ ከሩሲያ ጋር የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ 80 ሺህ የሚገመት የጦር መሳሪያን በማስገኘት ጦርነቱን በድል እንዲወጡ አስችሏቸዋል፡፡
በጦርነቱ ወቅትም የውጪ ዜጋን ጭምር በመጠቀም ኢትዮጵያ የብዙ ሺህ ዓመታት ታሪክ ያላት ሉዓላዊት ሀገር መሆኗን፣ ማንም ሊወራት እንደማይችል በዚያ ዘመን በነበሩ ታዋቂ የአውሮፓ ጋዜጦች በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲታተሙ አድርገዋል፡፡ አጤ ምኒልክ የውጪ ግንኙነታቸውን ቀደም ብሎ ስልጣኔ ለማስፋፋት፤ በጦርነቱ ጊዜ ደግሞ በበላይነት ለማጠናቀቅ ተጠቅመውበታል፡፡
አፈወርቅ ገብረየሱስ “አጤ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘ-ኢትዮጵያ” በሚል መጽሐፋቸው እንደከተቡት ንጉሡ በስልጣን ዘመናቸው ማብቂያ ኢትዮጵያውያን ውስጣዊ አንድነታቸውን አጠናክረው ሀገሪቱን ከውጪ ጠላት እንዲጠብቁ ምክር አስተላልፈዋል፡፡ በምክራቸው “እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ፣ በምቀኝነት ርስ በራሳችሁ ተዋግታችሁ ታላለቃችሁ በቀር ሀገራችንን ለሌላ ለባዕድ አትሰጧትም” ብለዋል፡፡ “…ልጀን አደራ ብዬ እሰጣችኋለሁና አሳድጉት፤ በብልሀት ምከሩት፣ በጉልበት አግዙት፤ በምክር ደግፉት፤ ልጀን አደራ ብየ መስጠቴ ከልጄ ጋር ኢትዮጵያን ጠብቁ ማለቴ ነው” በማለትም አሳስበዋል፡፡
የንጉሡ የአደራ ቃል ተግባራዊ አለመደረጉን የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ተናግረዋል፡፡ ሀገሪቱም በጥቅም ፖለቲካ መወጠሯን አንስተዋል፡፡ የሴራ ፖለቲካው ኢትዮጵያን የሚያሳንስ፣ ጥቅሟን የሚያሳጣ፣ ሕዝቦቿንም የሚያንኳስስ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ አቶ የሺዋስ የዓድዋን መንፈስ በመላበስ የኢትዮጵያዊነትን ትልቅ ስዕል ይዞ ለጋራ ስኬት መሥራት እንደሚገባ መክረዋል፡፡
መምሕሩ እንዳሉት የኢትዮጵያውያንን የጋራ ትግል የሚፈልጉ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለአብነትም ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና የኢትዮ-ሱዳንን ጉዳይ አንስተዋል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵ እጅግ በጣም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ድልን የሚያጎናጽፍ ነው፡፡ በማንኛውም መንገድ ይሕንን ሀገራዊ ፕሮጀክት ለማዘግየት የሚደረገውን ጥረት በአግባቡ በመረዳት ሁሉን አቀፍ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅ አንስተዋል፡፡
ከሱዳን ጋር የተፈጠረውን ችግርም በተጠና መልኩ መቀልበስ እንደሚገባ ነው ያስታወቁት፡፡ ለዚህም ሕዝባዊ አንድነትን በደንብ በማጠናከር የኢትዮጵያን መንግሥት ማገዝ ይገባል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ውስጣዊ አንድነትን እና የተጠና የውጪ ዲፕሎማሲን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleኢትዮጵያውያን በጋራ በመቆም ለሀገራቸው የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢፌድሪ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ጥሪ አቀረቡ፡፡
Next articleየተለያዩ የቅጥር ማስታዎቂያዎች ጐንደርና ደብረ ማርቆስ