አድማስ ሁለገብ የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኀበራት ዩኒዬን ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረገ ነው።

196
አድማስ ሁለገብ የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኀበራት ዩኒዬን ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረገ ነው።
ባሕር ዳር፡ የካቲት 07/2013 ዓ.ም (አብመድ) አድማስ ሁለገብ የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኀበራት ዩኒዬን ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ማስልጠኛ ተቋማት በተለያዩ የሙያ መስኮች ለተመረቁ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን አብመድ ከቦታው ተገኝቶ አረጋግጧል።
ወጣት ፈለጉሽ የኔት በአድማስ ሁለገብ የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኀበራት ዩኒዬን በሽመና ዘርፍ ተቀጥረው ከሚሠሩ ወጣቶች አንዷ ናት። ዩኒዬኑ ለእሷና ለበርካታ ወጣቶች በእንጅባራ ከተማ የተለያዩ ፋብሪካዎችን በመክፈት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ነው የገለጸችው። የኬሚስትሪ ምሩቅ መሆኗን የተናገረችው ወጣት ፈለጉሽ በዩኒዬኑ የሥራ ዕድል ከማግኘቷ በፊት ሥራ አጥ በመሆን ብዙ ጊዜዋን ከቤቷ ስታሳልፍ እንደነበር አስረድታለች።
በአድማስ ሁለገብ የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኀበራት ዩኒዬን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆኗ ደግም ሥራ በማጣት ሲደርስባት የነበረውን መጨናነቅ በማስወገድ ከሥራ ቦታ እንድትውልና ተጠቃሚ ለመሆን እንዳስቻላት ተናግራለች።
“ዩኒዬኑ የአካባቢውን ኅብረተሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው” ያለችው ወጣቷ እሷም ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም ያላትን እውቀት ለዩኒዬኑ ለማበርከት ዝግጁ መሆኗን አስረድታለች።
ሌላው በዩኒዬኑ የሥራ እድል የተፈጠረለት ደግሞ ወጣት በላይ ጥላሁን ነው፡፡ ወጣቱ በከረጢት ማምረቻ ፋብሪካ ተቀጥሮ እየሠራ ነው፡፡ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የሥራ ዕድል የተፈጠረለት መሆኑን ያስታወሰው ወጣት በላይ ወደ ሥራዉ ከመግባቱ በፊት የሙያ ስልጠና እንደተሰጠውም ተናግሯል። ይህ ደግሞ ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ እንዳገዘዉም ጠቁሟል።
የአድማስ ሁለገብ የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኅበር ዩኒዬን ቦርድ ሰብሳቢ ቀለሙ ጥሩነህ እንደገለጹት የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኀበራት ዩኒዬን በ1996 ዓ.ም አምስት ወረዳዎችን ማዕከል በማድረግ በ16 መሠረታዊ ማኅበራት እና በ855 ሺህ ብር ሥራ ጀምሯል።
ዩኒዬኑ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ እድገት እየታገዘ መሆኑን ያስረዱት የቦርድ ሰብሳቢው በአሁኑ ወቅት 245 ዜጎችን የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ አድርጓልም ብለዋል። ሁሉም ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ሥራ ሲጀምሩ ደግሞ ተጨማሪ 200 ሥራ ፈላጊዎችን መቅጠር እንደሚችል አስርድተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው-ከእንጅባራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ኢትዮጵያ እና ሱዳን ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን አስከብረው በትብብር ከመሄድ የተሻለ አማራጭ የላቸውም” ሱዳናዊ ፕሮፌሰር ሙሃመድ ሳላህ
Next articleበኩር ጋዜጣ የካቲት 08/2013 ዓ/ም ዕትም