የደብረብርሃን – ደነባ – ለሚ መገንጠያ እና ጅሁር – ደነባ የአስፋልት መንገድ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

587
የደብረብርሃን – ደነባ – ለሚ መገንጠያ እና ጅሁር – ደነባ የአስፋልት መንገድ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 05/2013 ዓ.ም (አብመድ) አካባቢው ከፍተኛ የጤፍ፣ የስንዴና የሰንጋ ምርት የሚገኝበት ቢሆንም መንገዱ አመቺ ባለመሆኑ የማሕበረሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ዝቅተኛ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አርሶ አደሮችና የንግዱ ማኅበረሰብ ምርትን ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በመቸገራቸውም የመንገዱ ደረጃ ወደ አስፋልት እንዲያድግ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያነሱ ነበር፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብ የዘመናት ጥያቄም ሰኔ 6/2012 ዓ.ም ምላሽ አግኝቷል፡፡
በዕለቱ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከደብረብርሃን-ደነባ-ለሚ መገንጠያ እና ጅሁር-ደነባ የአስፓልት መንገድ ግንባታን አስጀምረዋል፡፡ 108 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ፕሮጀክቱ መንግሥት በሚሸፍነው 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የሚሠራ ነው፡፡ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ድርጅት ግንባታውን በአራት ዓመታት ለማጠናቀቅ የውል ስምምነቱን ተፈራርሟል፡፡ የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅም የነበረውን የትራንስፖርት ችግር እንደሚቀርፍ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የምንገዱ መሠራት ባሶና ወራና፣ እንሳሮ፣ አብቹና ኘአ፣ ሲያ ደብርና ዋዩ እንዲሁም ሞረትና ጅሩ ወረዳዎችንም ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ደብረብርሃን እና አካባቢው ላለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረውም የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ታደሰ ገብረጻድቅ ተናግረዋል፡፡ ይሕንን ታሳቢ በማድረግም የዞኑ አስተዳደር ቀደም ብሎ የግንባታ ግብዓት ማዘጋጃ (ኳሪ ሰይት) እና የካምፕ መገንቢያ ቦታ ማስረከቡን አመላክተዋል፤ በግንባታ ወቅት የወሰን ማስከበር ችግር እንደማይገጥምም ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የግንባታ ማስጀመር እንቅስቃሴው በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑን አንስተዋል፤ ይህም የመዘግየት ስጋት መፍጠሩን ነው ያስረዱት፡፡ አቶ ታደሰ እንዳሉት የአካባቢው ማኅበረሰብ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ በጥራት እንዲጠናቀቅ ጥያቄዎችን እያነሳ ነው፡፡ በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት ለፕሮጀክቱ መሳካት በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የማዕከላዊ ሪጅን ቡድን መሪ ኢንጅነር ተስፋዬ አንተንይስሙ እንዳሉት ግን ግንባታውን ለማስቀጠል ጥሩ የሥራ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ለአማካሪ ድርጅት መኖሪያ፣ ካምፕና ቢሮ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች መሟላታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ማሽኖች ገብተው የተመረጠ አፈርና ድንጋይ ማምረት መጀመራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ኮንትራክተሩ የዲዛይን ሥራውን በወቅቱ ማጠናቀቁንም ነው ያስታወቁት፡፡
በዚህ ጊዜ የፕሮጀክቱ አማካሪ ድርጅት የዲዛይን ክለሳ እያደረገ ሲሆን እስካሁን 60 ኪሎሜትር ገደማ ክለሳ መሠራቱን አስታውቀዋል፡፡ እንጅነር ተስፋዬ በአማካሪ ድርጅት ምልመላ በመዘግዬት እና ፕሮጀክቱ እንደተፈረመ ክረምት በመግባቱ ምክንያት የግንባታ ማስጀመሪያ ጊዜ መራዘሙን ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ ግን ግንባታው መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ንዑስ ተቋራጭ ለማስገባት ማቀዱን አመላክተዋል፤ እየተከናወነ ያለውን የንዑስ ተቋራጭ መረጣም አማካሪ ድርጅቱ እየተከታተለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የባለስልጣኑ የማዕከላዊ ሪጅን ቡድን መሪ ኢንጅነር ተስፋዬ ንዑሳን ተቋራጮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡ በፕሮጀክቱ የታዬ መዘግየት ባይኖርም በሚፈለገው መልኩ እንዲጠናቀቅ ሁሉን አቀፍ ርብርብ እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡ ኢንጂነር ተስፋዬ እንዳሉት የአካባቢው መልክዓምድራዊ አቀማመጥ ከፍተኛ የአፈር ሙሌት፣ የተፋሰስ ሥራ እንዲሁም የክትትልና ቁጥጥ ሥራ የሚያስፈልገው ነው፡፡ የአስፓልት መንገዱ ያለምንም የጥራት ችግር በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ቅርብ ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየገንዘብ እጥረት የባሕር ዳርን ስታዲዬም ጣሪያ እንዳይለብስ አድርጎታል፡፡
Next articleኅብረተሰቡ የአማራ ክልል የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አደረጃጀትና አሠራርን በመረዳት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ ቀረበ፡፡