ዩኒቨርሲቲዎች የሚያካሂዷቸውን ጥናትና ምርምሮች ወደ ተግባር ለመቀየር በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባ ምሁራን አሳሰቡ፡፡

207
ዩኒቨርሲቲዎች የሚያካሂዷቸውን ጥናትና ምርምሮች ወደ ተግባር ለመቀየር በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባ ምሁራን አሳሰቡ፡፡
ባሕር ዳር ፡ የካቲት 04/2013 ዓ.ም (አብመድ) ዩኒቨርሲቲዎች የሚያካሂዷቸውን ጥናትና ምርምሮች ከሀገር በቀል እውቀት ጋር በማቀናጀት ለሀገር ልማት ከመጠቀም አንፃር ክፍተቶች መኖራቸው ይነገራል፡፡ እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት የሚያስችል ስልጠና ለዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በባሕር ዳር ከተማ እየተሰጠ ነው፡፡
በስልጠናው እየተሳተፉ የሚገኙት የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት እንደገና አበበ (ዶክተር) በዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮች ከኅብረተሰቡ ችግር የሚመነጩ፣ የሀገሪቱን ፖሊሲ ማዕከል ያደረጉ፣ ችግር ፈቺና እውቀትን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችሉ መሆን እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
አሁን በኢትዮጵያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ግን ጥናቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር ብዙ ሥራ ሊሠራባቸው እንደሚገባ አንስተዋል፡፡ እየተሰጠ የሚገኘው ስልጠናም ክፍተቶችን ለመለየት የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ቶውፊቅ ጀማል (ዶክተር) በዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር መነሻ ሃሳቦች ከኢንዱስትሪዎች መነሳት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡ ኢንዱስትሪዎችም ለጥናትና ምርምሮች ትኩረት በመስጠት የጥናቱን ሳይንሳዊ ግኝት ወደ ተግባር መቀየር እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች ለብቻ የትምህርት ተቋማት ለብቻ በመጓዝ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ እንደማይቻልም አስገንዝበዋል፡፡
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ያለው እንዳወቅ (ፕሮፌሰር) ከዚህ በፊት በሚሰሩ ጥናትና ምርምሮች ኅብረተሰቡን እንደ ተቀባይ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ እንደ አቀባይ አድርጎ የማሰብ አካሄድ እየቀረ ነው ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ሀገር በቀል ጥበብን በጥናትና ምርምር በማዳበር ለሀገር ልማት የጎላ ሚና እንዲያበረክቱ በፖሊሲ ተካቶ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊችም የምሁራንን እውቀት በአግባቡ በመጠቀም ለሀገር ልማት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው ፕሮፌሰር ያለው ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- በአዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleብሔራዊ የመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ ተኮር የምክክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።
Next articleየገንዘብ እጥረት የባሕር ዳርን ስታዲዬም ጣሪያ እንዳይለብስ አድርጎታል፡፡