ብሔራዊ የመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ ተኮር የምክክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።

221
ብሔራዊ የመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ ተኮር የምክክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ባሕር ዳር፡ የካቲት 05/2013 ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያ ከዘመናዊ የሀገረ መንግሥት ምስረታ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ከተዋወቁት ጉዳዮች ውስጥ መንግሥታዊ የአገልግሎት ተቋማትን ማደራጀትና ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ነው፡፡
ተቋማትን የማደራጀት፣ የሚመሩባቸውን ሕግጋትና ደንቦች የማውጣት፣ ሠራተኛና ሃብት በመመደብ ወደ ሥራ በማስገባት አገልግሎት መስጠትን የመንግሥት ዋነኛው ኀላፊነት ተደርጎ ከተወሰደ ረጅም ዘመን አስቆጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ ተቋማቱ ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ የገዥው ሥርዓት አገልጋይ ሆነው ቆይተዋል፡፡
ከሀገራዊ ለውጡ ጋር ተያይዞ በመንግሥት ከተወሰዱ መሰረተ ሰፊ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች አንዱ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ዘርፍን ከማንኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብና ተጽዕኖ ነጻ ሆኖ ለዜጋው ክብር የሰጠ፣ ግልጽ፣ አሳታፊ፣ ውጤታማና ተጠያቂ የሆነ ሰላማዊ ተቋማትን እንዲገነቡ ማስቻል ነው፡፡
በሂደቱና ውጤቱም የዘርፉ የሥራ ኀላፊዎችና ፈጻሚዎችም ለዜጋው አገልግሎት በመስጠታቸው ክብር የሚሰማቸው፣ እነሱም በዜጋው የሚታመኑና የሚከበሩ እንዲሆኑ በማስቻል በሕዝብና መንግሥት መካከል መተማመንና መግባባት እንዲያድግ ያደርጋል፡፡ ይህንን ለሀገራዊ እድገት ፋይዳው የጎላ የሆነውን አስተሳሰብ መነሻ ያደረገው እና የብሔራዊ ምክክር አካል የሆነው የመንግሥት የአገልግሎት ሰጪ ዘርፍ ተኮር ምክክር በመላ አገሪቱ በተከታታይ ይካሄዳል ተብሏል፡፡
የዚህ ምክክር ዋና ዓላማ በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን መለየት፣ መፍትሄ ማስቀመጥና እርምጃ እንዲወሰድ ግብዓት በመስጠት የአገልግሎት ዘርፉ ዘመናዊ፣ ተደራሽና የሕዝብ ይሁንታ ያለው አገልጋይ መንግሥት መገንባት ነው፡፡ በዚህ መነሻ ይህንን የመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ ተኮር ምክክር ለማስፈጸም እንዲቻል በ6 ክላስተሮች ከዞን እስከ ወረዳ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ከ795 በላይ የሆኑ ወረዳዎች የሲቪል ሰርቪስ መዋቅር የሥራ ኀላፊዎች በመጀመሪያው ዙር ከየካቲት 05 እስከ 07/ 2013 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ይሰጣል፡፡
ከመድረኩ በኋላም በየወረዳው የሚገኙ የመንግሥት መዋቅር የሥራ ኀላፊዎችና ፈጻሚዎች የምክክር መድረክ ይካሄዳል ተብሏል።
ዘጋቢ:- ደጀን አምባቸው – ኮምቦልቻ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየአማራ እና የሱማሌ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች የሕዝቦችን ትስስር እና አብሮነት ለማሳደግ በጅግጅጋ ከተማ መከሩ፡፡
Next articleዩኒቨርሲቲዎች የሚያካሂዷቸውን ጥናትና ምርምሮች ወደ ተግባር ለመቀየር በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባ ምሁራን አሳሰቡ፡፡