የአማራ እና የሱማሌ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች የሕዝቦችን ትስስር እና አብሮነት ለማሳደግ በጅግጅጋ ከተማ መከሩ፡፡

221
የአማራ እና የሱማሌ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች የሕዝቦችን ትስስር እና አብሮነት ለማሳደግ በጅግጅጋ ከተማ መከሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 05/2013 ዓ.ም (አብመድ) በሱማሌ ክልል በርካታ ቁጥር ያለው አማራ መኖሩን በመገንዘብ የሶማሌ ክልል ሬዲዮና ቴሊቪዥን ድርጅት የአማርኛ ቋንቋ ክፍል በማደራጀት መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህም በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን የርስ በርስ ግንኙነት ይበልጥ እያጠናከረ ነው ተብሏል፡፡ የሱማሌኛ ቋንቋን እና የሕዝቦችን ትስስር ለማሳደግ አማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በተያዘው ዓመት መጨረሻ ስርጭት ለመጀመር እየሰራ ባለው የቅድመ ዝግጅት ሥራ የክልሉን ድጋፍ ጠይቋል፡፡
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ የሱማሌና የአማራ ክልል ሕዝቦች ግንኙነት ዘመናትን የተሻገረ እና በአብሮነት የቆመ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ በሱማሌ ክልል አሁን ያለው የለውጥ አመራር በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ማንነታቸው ተጠብቆ ሀብት ንብረት የማፍራት እና ዲሞክራሲያዊ መብታቸው ተከብሮ እየኖሩ መሆኑን ትልቅ ግብ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
በሁለቱ ክልሎች መካከል የሚኖረው ግንኙነት ለኢትዮጵያ ጠቃሚና ስትራቴጅክ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ገደማ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች በማንነታቸው ጥቃት ሲደርስባቸው፣ ሲገደሉና ሲፈናቀሉ በሱማሌ ክልል ግን ይህ ድርጊት ፈጽሞ ያልተሰማ መሆኑ በአርአያነት ተጠቅሷል፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ክብርና እውቅና በመስጠት በተሰራው ሥራ እንደ ሀገር አርአያነት ያለው የተግባር ሥራ በመሆኑ የአማራ ክልል መንግሥት እውቅና እንደሚሰጥ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የኮምዩኒኬሽን ሥራው ላይ ክልሉ የሄደበት ርቀት እና ያመጣው ለውጥ ውጤት በመሆኑ ከዚህ ልምድ መወሰዱ ተገቢ እንደሆነም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅትን ዓለም አቀፍ እና ተወዳዳሪ ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ አቶ ግዛቸው ጠቅሰዋል፡፡ በተያዘው ዓመት መጨረሻ ከአምስቱ የፌዴራል የሥራ ቋንቋዎች አንዱ በሆነው የሱማሌኛ ቋንቋ ስርጭት ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት መጀመሩንም አስታውቀዋል፡፡ ይህም ቋንቋውን ከማሳደግ ባሻገር የማኅበረሰቡን ትስስር ይበልጥ ማሳደግ ተቀዳሚ ዓላማ ያደረገ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
የሱማሌ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ አሊ በደል ሙሀመድ የሱማሌና የአማራ ሕዝቦችን ትስስር የቆየ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የተጀመረውን ሁለንተናዊ ግንኙነት ዘላቂ በማድረግ የሕዝቦችን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማሳደግ ሥራዎች መጀመራቸውንም ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በርካታ ቁጥር ያለው አማራ መኖሩን በመገንዘብ የሱማሌ ክልል ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የአማርኛ ቋንቋ ክፍል በማደራጀት መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ወደፊትም ክልሉ እያስገነባ ያለው አዲሱ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ሲጠናቀቅ አሁን እየተሰራጨ ያለውን የአማርኛ ቋንቋ በስፋት ለማካተት በእቅድ መያዙን ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
የአብመድ የሱማሌኛ ቋንቋን በማካተት ዜናና ፕሮግራም ለመጀመር የያዘው እቅድ የሚመሰገን እና ለሱማሌ ሕዝብ እና ለቋንቋው እድገት የሰጠውን ትልቅ ቦታ እንደሚያሳይም ጠቅሰዋል፡፡
የሶማሌ ክልል ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በሶማሌኛ፣ በኦሮሚኛ እና በአማርኛ ቋንቋዎች ለአድማጭ ተመልካቹ መረጃዎችን እያደረሰ ነው፤ ጣቢያው በየዕለቱ ከምሽቱ 12፡00 እስከ 1፡00 የአማርኛ ፕሮግራሞችን እና ዜናዎችን ለአድማጭ ተመልካቹ ያደርሳል፡፡ የሥራ ኀላፊዎቹ ከውይይታቸው መጠናቀቅ በኋላ የክልሉን የመገናኛ ብዙኃን የሥራ እንቅስቃሴ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ጋሻው ፈንታሁን-ከጅግጅጋ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleሶስት አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው ተጠናቆ ለኢንቨስትመንት ዝግጁ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
Next articleብሔራዊ የመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ ተኮር የምክክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።