
ሶስት አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው ተጠናቆ ለኢንቨስትመንት ዝግጁ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 05/2013 ዓ.ም (አብመድ) በሶስት ክልሎች የሚገኙ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው ተጠናቀው ለኢንቨስትመንት ዝግጁ መሆናቸውን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ልማት ዳይሬክተር አቶ አያልነህ አባዋ እንደገለፁት፣ በፓይለት ደረጃ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች የተገነቡ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ዋና ዋና መሰረተ ልማቶች ተሟልተውላቸው ለኢንቨስትመንት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ፓርኮቹ ባለሀብቶችን አስገብቶ ለማሰራት ምቹ ሁኔታ የተፈጠረላቸው ሲሆን፤ የፓርኮቹ ቀሪ ስራዎች በውስጣቸው ፋብሪካዎች ሲስፋፉ የሚሟሉ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት በአማራ ክልል የተመረቀው የቡሬ ከተማ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ስራ የገባ ሲሆን፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች የተገነቡት ፓርኮችም በቅርቡ እንደሚመረቁ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
ይሁንና በትግራይ ክልል የሚገነባው ኢንዱስትሪ ፓርክ በበጀት እጥረት ሳቢያ ሼድ ያልተሰራበት በመሆኑ ባለሀብቶች እንዳልገቡበት ተናግረዋል፡፡
በአራቱም ክልሎች የሚገኙት ፓርኮች ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገቡ ለ400 ሺህ ቋሚ እና ለ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ የስራ እድል ይፈጥራሉ ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡
አግሮ ኢንዱስትሪዎቹ የተገነቡት በዋናነት ግብርናን ከኢንዱስትሪ ዘርፍ ጋር በማስተሳሰር የግብርናውን ሴክተር ለማዘመን በማለም እንደሆነም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
በዚህም ሂደት ግብርና የኢንዱስትሪ ግብዓት ፍላጎቱን ከማሟላት ባለፈ የአነስተኛ ማሳ አርሶ አደሮች ገበያን ፍላጎት መሰረት አድርገው እንዲያመርቱ ያስችላሉ ብለዋል ኃላፊው፡፡
በተጨማሪም አግሮ ኢንዱስትሪዎቹ በሸማቹና በገበሬው መካከል ያለውን ረጅም የንግድ ሰንሰለት በማሳጠር ገበሬው የምርቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ፋይዳቸው የጎላ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ፓርኮቹ በገጠር የኢንዱስትሪ ልማትን በማስፋፋት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲመጣ በማድረግ በተለይ ለባለሀብቶች ወጪ ቆጣቢ ምቹ የኢንቨስትመንት የስራ ቦታ ይፈጥራሉ ተብሏል፡፡
የአራቱ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የግንባታ ወጪ 30 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በአንድ ፓርክ ላይም ከ80 እስከ 100 ፋብሪካዎች ማቋቋም እንደሚቻል መገለጹን የዘገበው ኢብኮ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ