ከ37 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት በመስኖ እርሻ ለማምረት እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

180
ከ37 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት በመስኖ እርሻ ለማምረት እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 05/2013 ዓ.ም (አብመድ) አርሶ አደር ጌታቸው ንጋቱ በምስራቅ ጎጃም ዞን የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ቆንተር ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ በመኸር እርሻ ከሚያመርቱት ምርት በተጨማሪ በመስኖ ሽንኩርት፣ ማንጎ፣ ብርቱካን፣ ቡናና ፓፓያ በማምረት ከቤት ፍጆታቸው ባለፈ ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ሽንኩርት በመስኖ እያለሙ ነው፡፡ ከዚህም ከ50 እስከ 70 ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅደዋል፡፡
ምርታቸውን የተሻለ ለማድረግም በበቂ መጠን የአፈርና የቅጠል (ዳፕ እና ዩሪያ) ማዳበሪያ መጠቀማቸውን ነግረውናል፡፡ የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ በማግኘታቸውም ከዚህ በፊት ከነበረው የሽንኩርቱ ቡቃያ ቁመና መልካም የሚባል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ አርሶ አደሩ እንዳሉት ከመስኖ እርሻ በሚያገኙት ገቢ እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ አርሶ አደሮች ከብድር ተላቀው ገንዘብ መቆጠብ ጀምረዋል፤ ልጆቻቸውን በአግባቡ እያስተማሩ ነው፤ ኑሮአቸውም እየተሻሻለ ነው፡፡
ሌላኛው አስተያየት የሰጡን አርሶ አደር ስለሺ ደምሴ እንዳሉት በየዓመቱ ለመስኖ አመች የሆነውን መሬታቸውን በማልማት ተጠቃሚ ናቸው፡፡ በዚህ ዓመትም ሽንኩርትን ጨምሮ ጌሾ፣ ማንጎ እና መሰል ቋሚ ተክሎችን እያለሙ ነው፡፡ በመስኖ እያለሙ ካሉት ግማሽ ሄክታር መሬት 70 ኩንታል ሽንኩርት ለማግኘት እቅድ አላቸው፡፡
የምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አቶ አንዳርጋቸው ልየው በዞኑ በ2013 ዓ.ም በአንደኛ ዙር በነባር 18 ሺህ 787 ሄክታር፣ በአዲስ 1 ሺህ 300 ሄክታር በአጠቃላይ 20 ሺህ 87 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከአራት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እተሰራ መሆኑን ነግረውናል፡፡ እስካሁንም 19 ሺህ 368 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል ብለዋል፡፡ አርሶ አደሮች ማሳቸውን ዘግይተው በሚደርሱ አዝዕርት በመሸፈናቸው አፈጻጸማችን 96 ነጥብ 34 በመቶ ብቻ ነው ብለዋል ኀላፊው፡፡ “ቀሪውን ማሳ በዘር ለመሸፈን ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው” ብለዋል፡፡
በእቅድ ከተያዘው 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እስካሁን 129 ሺህ 635 ኩንታል ምርት ተሰብስቧል፡፡ የሁለተኛ ዙር መስኖን ውጤታማ ለማድረግም በአቅራቢ ድርጅቶች በኩል ምርጥ ዘር፣ የቅጠል እና የአፈር ማዳበሪያ (ዩሪያ እና ዳፕ) እየቀረበ ነው ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከፍተኛ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባለሙያ አቶ አወቀ ዘላለም በ2013 ዓ.ም በአንደኛ እና በሁለተኛ ዙር መስኖ እርሻ 248 ሽህ 20 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 37 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል፡፡ እስካሁን 216 ሺህ 736 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል ብለዋል፡፡ ምርቱን የተሻለ ለማድረግም 226 ሽህ 736 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን ባለሙያው ነግረውናል፡፡ የመስኖ ፕሮጀክቶች በወቅቱ አለመጠገን ለመስኖ እርሻ ልማቱ ዋነኛ ችግር እንደነበር አንስተዋል፡፡ እስካሁንም ከአንደኛው ዙር መስኖ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
በመስኖ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ይሆናሉም ተብሏል፡፡ እንደ ባለሙያው መረጃ ሁለተኛ ዙር መስኖን በውጤት ለማጠናቀቅም ኮንፈረንሶች ተካሂደዋል፤ አርሶ አደሮች ተለይተው ስልጠና ተሰጥቷል፤ የዞንና የወረዳ ግብርና ባለሙያዎችም ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡
የአርሶ አደሮቹ የመስኖ ምርት በተሻለ ዋጋ ለገበያ እንዲቀርብ ዩኒየኖችና ኅብረት ሥራ ማኅበራትን የማጠናከር ሥራ እየሰሩ መሆኑን አቶ አወቀ ተናግረዋል፡፡ “አርሶ አደሮች የተሻሻሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎችን እንዲጠቀሙ ለማድረግ ምርጥ ዘር የማራባት ሥራዎችን እየሰራን ነው” ብለዋል ባለሙያው፡፡ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ የማይመረቱ ምርጥ ዘሮችን ዩኒየኖች በተመጣጠነ ዋጋ እንዲያቀርቡ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮች አፈራርቀው በመዝራት በመስኖ የሚመረቱ ሰብሎች በበሽታ እንዳይጠቁና በተባይ እንዳይበሉ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል ባለሙያው፡፡
አርሶ አደሮች ያላቸውን መሬት በመስኖ በማልማት ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ አለባቸውም ነው ያሉት፡፡ ሁለተኛ ዙር መስኖ የመሬቱ እርጥበት ሳይለቅ ማከናወን ተገቢ በመሆኑ እስካሁን 3 ሺህ 427 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ በ2012 ዓ.ም በአንደኛና በሁለተኛ ዙር ከ220 ሽህ 600 ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን ከ30 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበሱዳን በተባባሰው ተቃውሞ የሀገሪቱ ዜጎች ለእስር እየተዳረጉ ነው፡፡
Next articleሶስት አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው ተጠናቆ ለኢንቨስትመንት ዝግጁ መሆናቸው ተገለጸ፡፡