
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የእናቶችና ህጻናት ሆስፒታል በአዲስ አበባ ተመረቀ።
ባሕር ዳር፡ የካቲት 04/2013 ዓ.ም (አብመድ) ሰባት የቀዶ ጥገና ክፍሎች፣ ከ 20 በላይ የተመላላሽ ህክምና አገልግሎት መስጫ ክፍሎች ከነ ሙሉ የህክምና ቁሳቁሶች የተሟሉለትና ከ400 በላይ የተኝቶ መታከሚያ ክፍል ያሉት ይህ ሆስፒታል አሁን አገልግሎት እየሰጡ ካሉት ሆስፒታሎች ይለያል ነው የተባለው፡፡ አገልግሎቱና ጥቅሙም የሰፋ እንደሚሆን ተገልጿል።
እስካሁን አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ሆስፒታሎች በሙሉ በከተማዋ እምብርት የተከማቹ ስለነበሩ እናቶች ለእርግዝና ክትትልና ወሊድ ርቀው እንዲሄዱ የነበረውን ሁኔታ ማስቀረቱ፣ በዚህም አንጋፋዎቹ ሆስፒታሎች ያጋጥማቸው የነበረውን የተገልጋይ ቁጥር ጫና በመቀነስ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ እድል ይፈጥራልም ተብሏል።
ሆስፒታሉ 400 አልጋ የያዘ መሆኑ ይህ ቁጥር አሁን በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉት ሌሎች 6 ሆስፒታሎች ያላቸው ለእናቶች የተመደበ አልጋ ተደምሮ ያለውን ቁጥር በሁለት እጥፍ ማሳደጉ፤ የመኝታ ክፍሎቹ በሙሉ የራሳቸው ሻወርና ሽንት ቤት ያለቸውና የምጥና ማዋለጃ ክፍሎች በሙሉ ለአንድ እናት አንድ ክፍል ሆኖ በመሠራቱ፤ በአጠቃላይ አስራ ስድስት የምጥና ማዋለጃ ክፍሎች ያሉት መሆኑ ከቀደሙት ሆስፒታሎች ልዩ እንዲባል አድርገውታል።
የስልጠና ማእከል ያለውና የመረጃ አያያዝ ስርዓቱ ሙሉ በሙሉ ከወረቀትና ካርድ ነጻ ነው የተባለው ሆስፒታሉ በእናቶችና ስነ-ተዋልዶ ጤና የልእቀት መዓከል እንዲሆን ተደርጓል፡፡ አሰራሮቹም ከሌሎች ሆስፒታሎች ጋር ትስስር እንዲኖረው ተደርጓል ተብሏል።
ህንፃው ከአሁን በፊት ለመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚነት ታስቦ ለ4 ዓመታት ሲገነባ የነበረና ያለ ምንም አገልግሎት የተቀመጠ ነበር ተብሏል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የለውጥ አመራር በከተማዋ የሚታየውን የእናቶች እና ህፃናት ህክምና አገልግሎት እጥረትና እንግልት በማጥናት ችግሩን ለመቅረፍ ይህ ተቋም ለእናቶች እና ህፃናት ሆስፒታልነት እንዲውል ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረትም በ700 ሚሊየን ብር በጀት አቧራውን አራግፎ፤ ዲዛይኑን አሻሽሎ፤ አዳዲስ ግንባታዎችን በመጨመር፤ እንዲሁም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አዘምኖ እና የህክምና መሳሪያ አሟልቶ ለአገልግሎት እንዲበቃ አድርጎታል ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ