
የ12ኛ ክፍል ሀገርአቀፍ ፈተና ከየካቲት 29 ቀን ጀምሮ ይሰጣል፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 04/2013 ዓ.ም (አብመድ) የትምህርት ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳለው የ2012 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 02/2013 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡
ፈተናውን 350 ሽህ ተማሪዎች ይወስዳሉ፡፡ ተፈታኞች ከየካቲት 22-24/2013 ዓ.ም በየትምህርት ቤቶች በመቅረብ የተሠራላቸውን የዲጂታል መታወቂያ እንዲወስዱ አሳስቧል፡፡
ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ(ዶ.ር) ፈተናው በመዘግየቱ የተማሪ ቤተሰቦችን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱም በዲጂታል ይሰጥ የነበረው ፈተና ታብሌቶቹ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ባለመቻላቸው የዘንድሮው በወረቀት እንዲፈተኑ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡
ትግራይ ክልልን በሚመለከት 12 ሽህ የሚሆኑ ሁሉም ተፈታኝ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤታቸው በመቅረብ ከቀጣዩ ሰኞ ጀምሮ ሪፖርት እንዲያደርጉ ያሳሰቡት ሚኒሰትሩ በክልሉ በሚገኙ 4 ዩኒቨርስቲዎች በትራንስፖርት በማጓጓዝ ፈተናቸውን እንደሚወስዱ ገልጸዋል፡፡
በመተከል የሚገኙ ተፈታኞችም የአካባቢው ጸጥታ እየተሻሻለ በመምጣቱ በ8 የመፈተኛ ጣቢያዎች እንደሚፈትኑ ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን – ከአዲስ አበባ