“የውጭ መገናኛ ብዙኃን ወኪል በመሆን ትሠራ ነበር የተባለችው ሉሲ ካሳ በሕጋዊነት ተመዝግባ አትንቀሳቀስም” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ

140
“የውጭ መገናኛ ብዙኃን ወኪል በመሆን ትሠራ ነበር የተባለችው ሉሲ ካሳ በሕጋዊነት ተመዝግባ አትንቀሳቀስም” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ
ባሕር ዳር፡ የካቲት 04/2013 ዓ.ም (አብመድ) ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን በዘገባ ወቅት ባልታወቀ ግለሰብ ጥቃት ደረሰባት በሚል የጠቀሳት ሉሲ ካሳ በኢትዮጵያ የውጭ መገናኛ ብዙኃን በሕጋዊነት የሚወክል ፍቃድ እንደሌላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንን ዋቢ አድርጎ አስታውቋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት የትኛውም ግለሰብ በደኅንነትና ነጻነት የመንቀሳቀስ መብቱ የተጠበቀ መሆኑንም ገልጿል።
ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ፍሪላንስ ጋዜጠኛ ሉሲ ካሳ በዘገባ ወቅት ከምትዘግበው ሁነት ጋር በተያያዘ ጥቃት ደርሶባታል በሚል እንዲሁም በኢትዮጵያ የሎሳንጀለስ ታይምስ፣ አልጀዚራና የኖርዌይ መገናኛ ብዙኃን ወኪል ናት ብሎ መረጃ አውጥቶ ነበር ።
የመረጃ ማጣሪያው ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የውጭ መገናኛ ብዙኃን በመወከል መንቀሳቀስ የሚፈልጉ ጋዜጠኞች በብሮድካስት ባለስልጣን በመመዝገብ ሕጋዊ መሆንና የመገናኛ ብዙኃን ይለፍ መታወቂያ መያዝ እንደሚጠበቅባቸው አስታውቋል።
ሆኖም ሉሲ ካሳ በብሮድካስት ባለስልጣን ሕጋዊ ምዝገባ አድርገው ከሚንቀሳቀሱ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ወኪሎች መካከል አለመሆኗን ነው ያስታወቀው።
ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ሉሲ ካሳ አልጀዚራን ጨምሮ ሌሎች የውጭ መገናኛ ብዙኃን በወኪልነት ትሠራ ነበር ብሎ ያወጣው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ገልጿል።
ቡድኑ መረጃ ከማሰራጨቱ በፊት የመረጃውን እውነተኝነት ግራና ቀኝ አጣርቶ ማውጣት እንደነበረበት ነው ያመለከተው።
በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ማንም ሰው በነጻነትና ደኅንነቱ ተጠብቆ መንቀሳቀስ እንደሚችል መደንገጉን ጠቁሟል፡፡ ቡድኑ በተሳሰተ ሁኔታ ያሰራጨውን መረጃ በአስቸኳይ እንዲያርም የመረጃ ማጣሪያው አሳስቧል።
Previous articleየኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በምርጫ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እያደረገ ነው።
Next articleየ12ኛ ክፍል ሀገርአቀፍ ፈተና ከየካቲት 29 ቀን ጀምሮ ይሰጣል፡፡