“የጎንደር እልፍኝ አቤት ስፋቱ ፣ የተመቸ ነው ቤተ መንግሥቱ።”

462
የጎንደር እልፍኝ አቤት ስፋቱ፣
የተመቸ ነው ቤተ መንግሥቱ።”
ባሕር ዳር፡ የካቲት 02/2013 ዓ.ም (አብመድ) ሙሽራዋን የመሞሸር ዘመን ደርሷል። ዘምኖ ማዘመን ቀርቧል። ለሁሉም ምቹ፣ ለሁሉም ዝግጁዋ እንግዶቿን ለመቀበል ሁሌም ዝግጁ ናት። በሚስጥራዊ ተራራዎች የተጋረደች፣ በአርባ አራት ታቦታት የፀናች፣ በፋሲል አብያተ መንግሥታት ግብረ ህንፃዎች የደመቀች፣ በጃንተከል ዋርካ ሥር በፍቅር የተጠለለች፣ በጥምቀተ ባሕር ሃይማኖት፣ ጀግንነት ፣ ታማኝነት፣ አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነትና አርቆ አሳቢነት የተጠመቀች፣ በቃል ኪዳን የፀናች፣ በጀግኖች የተጠበቀች፣ አልሞ የሚተኩስ፣ ፈትፍቶ የሚያጎርስ፣ አውልቆ የሚያለብስ፣ መከራን አሻግሮ ከደስታ የሚያደርስ ሕዝብ ያለባት-ጎንደር።
ጠቢባን ተቀኙባት፣ ሊቃውንት አዜሙባት፣ ጀግኖች ፈለቁባት፣ ነገሥታት ነገሡባት፣ ያዩዋት በትዝታ የሚባዝኑባት፣ ያላዩዋት ያዩዋት ዘንድ የሚመኟት ሙሽሪት ጎንደር። ቀድማ የከተመች፣ አስቀድማ የዘመነች፣ የስልጣኔ አውታር የሆነች፣ ትናትንና ዛሬን አጣምራ የያዘች ናት።
የአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ሲጋመስ ኢትዮጵያ ጦርነት ያዘገዬውን ስልጣኔዋን ለማምጣት ጥረት ማድረግ ጀመረች። የትብብር ዘመኗን ለመመለስም ተንቀሳቀሰች። በአፄ ገላውዲዎስ የሚመራውን የኢትዮጵያ ጦር ለማገዝ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት የፖርቹጋል ሚሲዮናውያን ሃይማኖታቸውን ያሰፉ ጀምረዋል። የሀገሬውን ቋንቋ ግእዝ እና አማርኛን አቀላጥፈው ይናገራሉ። በቤተመንግሥት ከፍተኛ ተቀባይነት ያላትን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ተቀባይነቷን ለማሳጣትና የእርሷን ቦታ ለመያዝ ጥረት ላይ ናቸው።
ወናግ ሠገድ ገላውዲዎስ ጉዳዩን በብልሃት እያዩ ተቀመጡ። የመጨረሻ እልባት ሳያገኝ ንጉሡ አለፉ። ዙፋኑን ሚናስ ተረከቡት። ኢትዮጵያን ለመውረር ስትቋምጥ የነበረችውን ቱርክ አስገበሩ። እሳቸውም ብዙ ሳይቆዩ አለፉ። የአፄ ሚናስ ልጅ አቤቶ ሰርፀድንግል በለጋ እድሜያቸው ነገሡ። አስታዋዩ ንጉሥ ጠላቶቻቸውን በስልትና በጀግንነት አሸነፉ። እንደ አባታቸው ሁሉ ቱርክን አስገብረው እስከ ኤደን ባሕረ ሰላጤ አስተዳዳሩ።
አቤቶ ሰርፀድንግል ለመንግሥታቸው ማረፊያ ይሆን ዘንድ ቤተ መንግሥት ማሠራት ወደዱ። ከእንፍራንዝ አጠገብ በጉዛራ ቤተመንግሥት አነፁ። ይሄም ቤተመንግሥት የመጀመሪያው ባለ ሦስት ወለል የአፍሪካ ቤተ መንግሥት ነው ይባላል። የጎንደር ዘመን ተቀየሰ። የመንግሥቱ መርጊያ ከዚያ አካባቢ እንደማይወጣ አመላካች መጣ። አቤቶ ሰርፀድንግልም አለፉ። የወንድማቸው ልጅ አቤቶ ያዕቆብ በሰባት ዓመታቸው ነገሡ። ልጃቸው ዘ ድንግል ለንግሥና ባለመብቃታቸው አመፅ እንዳያስነሱ ወደ ግዞት ተላኩ። የሠባት ዓመቱ ንጉሥ እድሜያቸው እየጨመረ ሄደ። በዙፋናቸው ሞግዚቶቻቸው እናታቸው እቴጌ ስና ማርያም እና ራስ ዘ ስላሴ እንዲያዙበት አልፈቅድ አሉ። በመላ ተይዘው ወደ ግዞት ወረዱ። የነገሥታት ዘር ካልነገሠ ሕዝቡ ስለማይገዛ አስቀድመው ወደ ግዞት የተላኩት ዘ ድንግል ነገሡ።
ንጉሡም የካቶሊክ ሃይማኖትን ተቀበሉ ተባለ። ይሄን የሰማው የሀገሬው ሰው ተቆጣ። በንጉሡ የተቀየሙት የቤተመንግሥት ባለሟሎች ከቤተ መንግሥት ወጡ። ጦር መሪው ራስ ዘ ስላሴ እና እቴጌ ስና ማርያም ወደ ደንቢያ ወረዱ። ሠራዊቱም ልቡ ይተከን ጀመር። ጳጳሱ አባ ጴጥሮስ ሕዝባቸውን አነቁ። ሕዝቡም ለእቴጌ ስና ማርያም እና ለራስ ዘ ስላሴ ገባላቸው። ከንጉሡ ያልወጣውና በእነ ራስ ዘ ስላሴ የሚመራው የሀገሬው ሰው ተጋጩ። የ ዘ ደንግል ዘመን ተፈፀመ። ያዕቆብ ድጋሜ ነገሡ። ንግሥናቸው ግን የተረጋጋ አልነበረም። እርሳቸውም አለፉ። አቤቶ ሱስንዮስ አፄ ሰርፀድንግል ባሰሩት ቤተመንግሥት ሡልጣን ሰገድ ቀደማዊ ተብለው ነገሡ። ወደ አክሱም ፅዮንም ሄደው ንጉሠ ፅዮን በሚል የንግሥና ስርዓታቸውን ከወኑ። የካቶሊክ ሚሲዮናውያን ያማክሯቸው ጀመር። በጣና ዳርቻም የማምለኪያ ቦታ ሰጧቸው። በዚያች ቦታም ቤተመንግሥት እንዲሠራ አደረጉ።
የጎንደር ዘመን ቀጠለ። የጣና ዳርቻው ቤተመንግሥት የወባ በሽታ የሚበረክትበት ሆነና ሕዝባቸውንና ሠራዊታቸውን ክፉኛ ጎዳው። ሌላ ቤተመንግሥት በደንቀዝ አሰሩ። የካቶሊክን ሃይማኖት ተቀበሉ። ነገር ግን የዘ ድንግል ታሪክ እንዳይደገም ስለሰጉ ሕዝቡ እንዲያውቅ አልፈለጉም ነበር። ባለቤታቸው እቴጌ ወልደ ሳዕላ አዲስ ሃይማኖት አልቀበልም ብለው ወደ ቆማ ሄዱ። ቆማ ፋሲለደስ ቤተክርስቲያንንም አሠሩ። የንጉሡም ሃይማኖት መቀየር ተሰማ። የተፈራው ደረሰ። ሕዝቡ ተቆጣ። ከዳቸው።
አቤቶ ፋሲል ከሕዝቡ ጋር ወገኑ። ሕዝቡም ወደዳቸው። “ፋሲል ይንገስ ሃይማኖት ይመለስ” ይባልላቸው ጀመር። ሱሱንዮስም ወደ ሕዝቡ ተመለሱ። ዙፋናቸውን ለልጃቸው ለአቤቶ ፋሲል አስረከቡ። እንዲህም ታወጀ እኮ፣ ፋሲል ነገሰኮ፣ ሃይማኖት ተመለሰኮ ተባለ። አስቀድሞ የተቀየሰው የጎንደር ዘመን ትክክለኛውን ሰው አገኘ። ንጉሡ ዓለም ሰገድ ፋሲል ካቶሊኮችን በፍቅር ወደሀገራቸው ሸኟቸው።
አምላክ ደጓን ምድር ተመለከታት። መልዕከተኛውንም በወፍ አምሳል ላከ። መልዕክተኛዋም “ጎ” ትነግሥ እያለች ትዘምር ጀመረች። መልዕክቱን የሰሙት ንጉሡ ፋሲል ቦታዋን ያገኙ ዘንድ በልባቸው አሰቡ። ይህች ገነተ እዝራ የሔኖክ ወይስ የያሬድ ትሆን እያሉ ያስቡ ነበር። ጊዜው ቀረበ። መልካሙ ምድር በመልካም የተፈጥሮ ካባ ተውቧል። መልካም ዘመን ቀርቧል። ዓለም ሰገድ ፋሲል አባታቸው ባሰሩት በደንቀዝ ቤተመንግሥት የማለዳ ፀሎታቸውን አደረሱ። ቁርሳቸውንም ቆረሱ። በሰገነቱም ተቀመጡ። አንድ አምሳለ ነብይ ጎሽ በአሻገር ያገሳል። ንጉሡ ተነሱ። ፈረሳቸውን ጭነው ወጡ። ጎሹን ተከተሉት። ጎሹም ሮጠ። ጎሹም በሩጫ ብዛት ውኃ ጠምቶት ነበርና ከአንድ ኩሬ ውኃ ሊጠጣ ወደደ። አንገቱን ደፋ። ንጉሡ ይወጉት ዘንድ ጦራቸውን ሰበቁ። ትንቢት ሊፈፀም ነበርና ንጉሡ ጦራቸውን በሰበቁት በኩል አንድ ቅዱስ አባት ታዩ። ቅዱሱ አባትም ንጉሡን ባረኳቸው። የዘመናት ትንቢት ተበሰረ። ሀገረ እግዚአብሔር የማመስገኛዋ ከተማ የተመረጠችው ሥፍራ ያቺ መሆኗን ነገሩት።
ንጉሡ ተደሰቱ። ለትንቢቱ መፈፀም ግብር አበሉ። በክብርና በሞገስም ወደ ቃልኪዳኗ ስፍራ አቀኑ። የኢትዮጵያ መናገሻዋ ተበሰረች። ዓለምን ያስደመምሙ የጥበብ ሥራዎች አረፉባት። የጌታ ማመስገኛዎች ታነፁባት። ጎንደር “ጉንደ ሀገር” የሀገር መሠረት፣ የሀገር ግንድ፣ ታላቅ ምድር፣ ያገር ቀንዲል ትባላለች። ጎንደር በዓለም ሰገድ ፋሲል እንደተቆረቆረች ቢነገርም ከዚያ አስቀድማ እንደነበረች ይነገራል።
“ማን ሀሰት ይለኛል እውነቱን ብናገር፣
የታሪክ አሻራ ዛሬም አለ ጎንደር” መናገሻዋ እመቤት ኢትዮጵያውያን በዋና ከተማነት በማገልገል የሚተካከላት አይገኝም ይሏታል።
የሲራራ ንግድ ማዕከል፣ የስልጣኔ ቀንዲል፣ የጥበብ ምድር፣ የጀግና እናት ጎንደር። ታይተው የማይጠገቡ፣ ታሪካዊና መንፈሳዊ ሥፍራዎች መገኛም ናት። ዓለም ሁሉ ሊያያት ይመኛታል ቀደምቷን ከተማ። ጎንደር በጥንታዊ የባለፀጎች ማረፊያ ማዕከልም ነበረች። ማዕከላቸውን ጎንደር ከተማን ያደረጉ ሦስት ዋና የሲራራ ንግድ መስመሮች ለረጅም ጊዜ ተዘርግተው እንደነበር ይነገርላታል።
አንደኛው መነሻውን ጎንደር አድርጎ ወገራ፣ ደባርቅ፣ ሊማሊሞ፣ ተከዜ፣ ሽሬና አድዋን በማለፍ ምፅዋ ደርሶ የሚመለሰው የሲራራ ንግድ መስመር፡፡ ሁለተኛው በጭልጋ፣ መተማንና ስናርን፣ ሱዳንን አልፎ ምስር (ግብፅ) ደርሶ የሚመለሰው መስመር፡፡ ሦስተኛው የንግድ መስመር ደግሞ በይፋግ፣ ጎጃም አድርጎ አባይን በመሻገር አናርያ፣ ካፋና ጃናጃሮ ድረስ የተዘረጋ ነበር ይባላል።
በጎንደር ከሩቅ ምሥራቅ፣ ከአውሮፓና ከሌሎች የሚነሱ ነጋዴዎች ከባሕር ወርደው ይመጡባት ነበር። የሲራራ ነጋዴዎች ግመሎቻቸውን እና አጋስሶቻቸውን ጭነው ይመጣሉ። በመናገሻዋ ይከትማሉ። ወርቅ፣ ብር፣ ዝባድ፣ ቡና፣ መስታውት፣ ጌጣጌጥ፣ ነፍጥ፣ ጨው፣ ወይን፣ ዘቢብ፣ የዝሆን ጥርስ፣ ዋንጫ፣ ጋሻና ሌሎችን ይገበያዩባት ነበር። የሲራራ ንግድ መናኸሪያዋ ፣ የስልጣኔ ቀንዲልና የኪነ ጥበብ ማህደር፣ የዘመናዊ አኗኗር ተምሳሌት፣ የጥበብ፣ የትምህርት፣ የፍልስፍና መነሻ ከተማዋ ጎንደር በዚያ ዘመን ነግዶ ለማትረፍ የተመኘ ሁሉ ምድሯን ይረግጣል፡፡
በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነገሥታቱ ዜና መዋዕል ፀሐፊ አዛዥ ሲኖዳ ስለ ጎንደር ሲፅፍ “በአህጉሩ ላመል ምንም የማይታጣባት” ብለዋታል። ካንቲን ዱለም የተባለ ፈረንሳዊ “የፈረንሳይ ገዢ ሆኖ ፓሪስን ያላየ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ጎንደርን ያላየ ሰው ዜግነቱ ጥያቄ ውስጥ ነው” ማለቱን አሰግድ ተስፋዬ ጎንደር የአፍሪካ መናገሻ በሚለው መፅሐፋቸው ከትበዋል።
ኢትዮጵያ “ዘ አንኖውን ላንድ” በሚል ርዕስ የፃፈው ሞንሩ ሀይ “የገነት አምሳያ የጥቁር ሕዝቦች ማማ” ብሏታል። የቦታ አቀማመጧ ለጦር ስልት መመቸት፣ የዓየሩ ተስማሚነት፣ ለንግድ አውታር ምቹ መሆንና ሌሎች ፀጋዎቿ ጎንደርን መናገሻ አድርገዋት ኖረዋል። የመናገሸዋ ከተማ ጎንደር በዚያ ዘመን ከዓለም የተውጣጡ ሰዎች ለመኖሪያነት የሚመርጧትና በጋራ የሚኖሩባት ከተማ ነበረች። የዚያ ዘመን ፍቅር ዛሬም ቀጥሏል። በፍቅር የሚኖሩባት ብዙዎች ናቸው።
በቅዱስ መንፈስ መሪነት የተመሠረተችው ጎንደር በጥበብ ተሠራች፣ በጥበብ ኖረች፣ በጥበብ ትኖራለች፣ በጀግኖች ትጠበቃለች፣ ዘመን ዘመንን አልፎ ከነፈ። ስልጡኗን ከተማ ሥርዓት አልመቻት እያለ መጣ። አስቀድማ የስልጣኔ ጉዞ የጀመረችውን እመቤት መንገዷን የሚያስቀጥል እያጣች ሄደች። ይልቁንም ይበድሏት ጀመር። እርሷም ትግስት የእርሷ ነውና በትግስት ትጠብቅ ጀመር። ዓመታት ተሸኙ። የሲራራ መናኸሪያዋ፣ የዓለም ነጋዴዎች መዳረሻዋ፣ እንኳን ሰዎቹ ግመሎቹ ሁሉ ይናፍቋት የነበረችው ጎንደር የንግድ መሥመሮቿ ሁሉ እየቀነሱ ሄዱ። የተዘጋጀውን የስልጣኔ ማዕድ የሚቆርስ ጠፋ። ከሥልጣኔዋ ጅረት የሚጠጣ አዲስ ዘመን የሚያመጣ ትፈልግ ጀመረች።
በአራቱም አቅጣጫ በረከትና ሀበት የሚገባላት ጎንደር ከደንቢያ ጤፍ፣ ከፎገራ ሩዙን፣ ከመተማና ሁመራ ሰሊጡንና ጥጡን፣ ማር፣ ወተትና ቅቤውን፣ ከወገራና ሰሜን ጃናሞራ ገብስና ባቄላውን፣ ከበለሳ ሽንበራውን ታስገባለች። የነጭ ወርቅ ምድር መገኛ ናትና ለዳግም ስልጣኔዋ መልካም እድል ነው። የዓለም ጎብኚዎች መዳረሻ መሆኗም ሌላኛው የልማት አማራጯ ነው። ጎንደር የተጫናትን ስርዓት አውርዳ አስቀድማ የጀመረችውን ስልጣኔ የቀጠለች ትመስላለች።
“የጀግናው ሹርባ መጣሉ በክብር መጣ ተመልሶ፣
አሃዱ አለች ጎንደር ደግሞ ልትሞሸር ዙፋኗ ታድሶ” እንዳለች ከያኟ ጎንደር ልትሞሸር ነው። ታሪካዊቷን ከተማ የመሞሸርና የታሪኳ ተካፋይ የመሆን ዘመን ደርሷል። ዘመናዊ ኢንዱስትሪዎች ይበዙባት ጀምረዋል። ለሁሉም ምቹና ዝግጁ የሆነችው ጎንደር አሁንም አይበቃትም። ተጨማሪ ትሻለች።
“እንኳን እናት አገር ትልቁን አደራ፣
ጎንደር ማተብ አለው ክደት እንዳይሰራ” እንደተባለ ሀገር ወዳዱ የጎንደር ሰው አቁማ የቆዬችውን ስልጣኔ ዳግም ትጀመረው ዘንድ ምኞቱና ተግባሩ ነው።
ቀደም ሲል በግመልና በአጋስስ የንግድ አውታር የነበረችው ጎንደር በዘመኑ ደግሞ የበለጠ የንግድ አውታር የምትሆን ናት። ቢሻት በኤርትራ ቀይ ባሕር፣ ቢሻት ስናር ንግዱን ማጧጧፍ ትችላለች። ቢፈልጉ በአየር አይሆንም ካሉ በምድር ስንዱ ናት ጎንደር። አስቀድማ በሰለጠነችው ከተማ ሰልጥነው የሚሰለጥኑ ብልህ ባለፀጋዎችን ትጠብቃለች። ይሂዱ ይዪዋት፣ በመንፈሷ ይታደሱ፣ ከማዕዷ ይቋደሱ፣ በስልጣኔዋ ከተማ በስልጣኔ ይገስግሱ።
“በለጋስ እጁ በደግነቱ፣
አይጠረጠር በጀግንነቱ፣
የጎንደር እልፍኝ አቤት ስፋቱ፣
የተመቸ ነው ቤተ መንግሥቱ” ብልሆች ሄደው ይዘምኑባታል። ሞኞች ባሻገር ያይዋታል። ብዙ አመሰራጮች፣ ለብልህ ባለፀጎች በጎንደር አለ።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየልጅነት ጋብቻን ለማስቀረት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next articleየሚቋቋሙ ፋብሪካዎችን እና የአርሶ አደሮችን የግብዓት አቅርቦት ትስስር ሊያግዝ የሚችል የትምህርት ክፍል መክፈቱን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡