የልጅነት ጋብቻን ለማስቀረት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡

303
የልጅነት ጋብቻን ለማስቀረት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 02/2013 ዓ.ም (አብመድ) የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) በ2018 (እ.አ.አ) በኢትዮጵያ ባደረገው ጥናት 50 ወረዳዎች የልጅነት ጋብቻ ጎልቶ ታይቶባቸዋል። በአማራ ክልል ደግሞ በ23 ወረዳዎች ችግሩ የከፋ እንደሆነ ይፋ አድርጓል። በዚህም 43 በመቶ ሴቶች የልጅነት ጋብቻ ፈጽመዋል። ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ በድኀነት ውስጥ ያሉ፣ ያልተማሩ እና በገጠር የሚኖሩ መሆናቸውን ድርጅቱ ይፋ አድርጓል።
በኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ወደ ትዳር እንዳይገቡ ህግ ይከለክላል፡፡ ወላጆች ይኼን ተላልፈው ልጆቻቸው ጋብቻ እንዲፈጽሙ ካደረጉ እንደሚጠየቁም በህጉ ላይ ተደንግጓል፡፡ ነገርግን በርካታ ወላጆች ህጉን ተላልፈው ልጆቻቸውን ለልጅነት ጋብቻ ሲያጋልጡ ይስተዋላል፡፡ በዚህም በርካታ ህጻናት ከትምህርታቸው ተስተጓጉለዋል፤ ያለእድሜያቸው ወልደው ባልጸና ጉልበት ልጅ ለማሳደግ ሲውተረተሩም ይታያሉ፤ ጥቂት የማይባሉት ደግሞ በወሊድ ምክንያት ላይመለሱ ይህን ዓለም ተሰናብተውታል፤ የቀሩት ደግሞ ለፌስቱላ ህመም ተዳርገው እንኳንስ ትዳራቸው ሊጸና ከቤተሰቦቻቸው ተገልለው እንዲኖሩ ይገደዳሉ፡፡
የልጅነት ጋብቻ ጉዳቱ በተጋቢዎች፣ በወላጆች እና በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይም ክንዱ የበረታ ነው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ በተለያዩ አካላት ትኩረት ተሰጥቶት ቢሰራም መቀነስ እንጅ ሙሉ በሙሉ ማስቆም አልተቻለም፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ እንደ ኀላፊዋ ገለጻ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው የተሳሳተ አመለካከት በክልሉ የልጅነት ጋብቻ በሰፊው እንዲፈጸም አድርጓል፤ ችግሩን ለመከላከል ሥራዎች እየተሰሩ ቢሆንም ውጤት ማስመዝገብ አለመቻሉን ነው የገለጹት፡፡ እንደ ኀላፊዋ ማብራሪያ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን የአመለካከት ችግር ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፤ በዚህም አንጻራዊ መሻሻሎች እየታዩ ቢሆንም የልጅነት ጋብቻ አሁንም ችግር ሆኖ መቀጠሉ አልቀረም፡፡
በተለይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን መግባቱን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ችግሩን አባብሶታል፡፡ የክልሉ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ችግሩን ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን ኀላፊዋ አብራርተዋል፡፡ በዚህም የረጅምና የአጭር ጊዜ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ለዞን እና ለወረዳ ባለሙያዎች እንዲሁም ለሥራ ኀላፊዎች የማስተዋወቅ ሥራ መሥራታቸውንም ነግረውናል፡፡
የልጅነት ጋብቻን በመከላከል ልጆች ትምህርታቸውን በትኩረት እንዲከታተሉ እስከ ቀበሌ ድረስ የተቀናጀ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የልጅነት ጋብቻ የሚያስከትለውን ጉዳት በትክክል ማስገንዘብ፣ የልጅነት ጋብቻ ሊፈጽሙ ባሉ ቤተሰቦች የማገጃ ደብዳቤ መስጠት፣ ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከፍትህ እና መሰል ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት፣ የእድሜ ምርመራ በማድረግ እና ታች ያለውን መዋቅር በማጠናከር ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡
ወይዘሮ አስናቁ እንዳሉት በብዛት በኢኮኖሚ ዝቅተኛ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው የልጅነት ጋብቻ እንዲፈጽሙ ያሰገድዳሉ፡፡ ይኼን ለመከላከል ኢኮኖሚውን የሚመሩ አካላት የትኩረት አቅጣጫቸውን በመለየት እንደዚህ አይነት ችግር ያለባቸውን ወላጆች ሊያግዙ ይገባል፡፡ የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ በበኩሉ ለችግር የተጋለጡ ህጻናት እና ወላጆች ራሳቸውን ለማስቻል ከአጋር አካላት ጋር እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ የልጅነት ጋብቻን ለማስቆም የችግሩን ውስብስብነት እና የሚያስከትለውን የከፋ ጉዳት በመረዳት ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ ኀላፊዋ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleአምባሳደር ነብያት ጌታቸው በአልጄሪያ የመድኃኒት ማምረቻ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያ መሰማራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ፡፡
Next article“የጎንደር እልፍኝ አቤት ስፋቱ ፣ የተመቸ ነው ቤተ መንግሥቱ።”