አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በአልጄሪያ የመድኃኒት ማምረቻ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያ መሰማራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ፡፡

117
አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በአልጄሪያ የመድኃኒት ማምረቻ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያ መሰማራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 02/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአልጄሪያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባለሙሉስልጣን አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በአልጄሪያ የመድኃኒት ማምረቻ ዘርፍ ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ካለው ከፍራተር ራዜስ የፋርማሲቲካልስ ኩባንያ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ ስላለው ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል ግንዛቤ አግኝተው ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት መዳረሻቸው እንዲያደርጉ ማበረታታትን ዓላማ ያደረገ ውይይት አካሂደዋል፡፡
አምባሳደር ነብያት ለኩባንያው ባለቤትና የሥራ ኃላፊዎች ባደረጉት ገለጻ የፋርማሲዮቲካል ዘርፍ በመንግሥት ቀዳሚ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡በዘርፉ ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የገበያ እድል እና በመንግሥት ስለሚቀርቡት የተለያዩ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያመረቱትን ምርት ለመሸጥ በኢትዮጵያ ካለው ሰፊ ገበያ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ስትራቴጂካዊ መገኛ ስፍራ ተጠቅመው ወደ ተለያዩ ገበያዎች በቀላሉ ለመድረስ እንደሚቻልና በምሥራቅና የደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ)፣ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ምርታቸውን ከቀረጥና ኮታ ነፃ ወደ አሜሪካ ገበያ እንዲያስገቡ የሚረዳው የአጎዋ ስምምነት የገበያ መዳረሻ እና የሌሎችም የገበያ ዕድሎች ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ተናግረዋል።
የኩባንያው ፕሬዚዳንትና ባለሃብት ዶክተር አብደልሃሚድ ሸርፋዊ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ዘርፉን ለማስደግ እያደረገች ያለችውን ጥረት እና ያለውን ከፍተኛ የገበያ እድል አድንቀዋል፡፡
በዘርፉ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያስችል የቅድመ-ኢንቨስትመንት ጉብኝት በቅርቡ እንደሚያካሄዱ ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ በኢትዮጵያ የፋርማስቲካል ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችሉ ውይይቶችን ከሀገሪቱ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር እያካሄደ መሆኑን አሳውቋል፡፡
በአልጀሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ካሁን ቀደም በፋርማሲዮቲካል ዘርፍ የኢንቨስትመንት ትውውቅ መርኃ ግብር በበይነ መረብ ማካሄዱ ይታወሳል፡፡ መረጃው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት ነው፡፡
Previous articleየደብረብርሃን-አንኮበር አስፋልት መንገድ ግንባታ ለምን ዘገየ? መፍትሔውስ?
Next articleየልጅነት ጋብቻን ለማስቀረት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡