
የደብረብርሃን-አንኮበር አስፋልት መንገድ ግንባታ ለምን ዘገየ? መፍትሔውስ?
ባሕር ዳር፡ የካቲት 02/2013 ዓ.ም (አብመድ) ታኅሳስ/2011 ዓ.ም የተጀመረው የደብረ ብርሃን – አንኮበር የአስፋልት መንገድ ግንባታ አፈጻጸም 65 በመቶ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
በ1 ቢሊዮን ብር ወጪ ግንባታው የተጀመረው ፕሮጀክቱ በ2 ዓመት እንደሚጠናቀቅ በማስጀመሪያው ወቅት ተጠቅሶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እንደተባለው ሳይሆን የመንገዱ ግንባታ መዘግየት ታይቶበታል፤ ለዚህም ባለስልጣኑ የተለያዩ ምክንያቶችን ጠቅሷል፡፡
በባለስልጣኑ የማዕከላዊ ሪጅን ቡድን መሪ ኢንጅነር ተስፋዬ አንተንይስሙ እንዳሉት ግንባታው ከተጀመረ በኋላ በደብረብርሃንና ጎረቤላ ከተሞች የዲዛይን ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ በማሻሻያው ፈጣን እድገት እያስመዘገበች ላለችው ደብረብርሃን ከተማ ሦስት ኪሎሜትር ርዝመት ያለው መንገድ ባለ 10 ሜትር የአካፋይ መንገድ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ በተመሳሳይ የጎረቤላ ከተማን ሳይነካ በ10 ሜትር ስፋት ብቻ እንዲገነባ ተወስኖ የተሠራው ዲዛይን ከሕዝብ ቅሬታ በማስነሳቱ በከተማ መሀል እንዲያልፍ መደረጉን ተናግረዋል፤ 19 ሜትር ስፋት እንዲኖረው ማስተካከያ መሠራቱንም አስታውቀዋል፡፡
በሁለቱ ከተሞች የመሠረተልማት አውታሮች አለመነሳት እና የወሰን ማስከበር ችግሮች መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡ በዚህም ተቋራጩ የጊዜ ማራዘሚያ ጥያቄ ማቅረቡን አመላክተዋል፡፡
ኢንጅነር ተስፋዬ የወሰን ማስከበር ችግርን እንደ አንድ ምክንያት ቢያነሱም የዞኑ አስተዳደር ግን ምክንያቱን ተገቢ አይደለም ብሎታል፡፡
የዞኑ አስተዳዳሪ ታደሰ ገብረጻድቅ እንዳሉት አዲሱ የካሳ ክፍያና መልሶ መቋቋሚያ አዋጅ ቢዘገይም ልማት እንዳይቋረጥ በሚል አርሶ አደሮች ካሳ ሳይከፈላቸው መሬታቸውን ለቀዋል፡፡ በተቋራጭና በመንግሥት አካላት የሚጓተተው ግምት ውስጥ ሳይገባ ያለካሳ መሬቱን የሰጠ አርሶ አደርን ምክንያት ማድረግ ተቀባይነት የለውም ሲሉ ዋና አስተዳዳሪው አብራርተዋል፡፡ በሕዝብ ዘንድ በሰንሻይን ተቋራጭ ላይ የሚነሳ የጥራት ችግርና የግንባታ መዘግየት እንዲስተካከልም ጠይቀዋል፡፡
የፌደራል መንገዶች ባለስልጣን የማዕከላዊ ሪጅን ቡድን መሪ ኢንጅነር ተስፋዬ ከሥራ ጥራት ጋር ለሚነሱ ስጋቶች በሰጡት ማብራሪያ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በተለይ አንኮበር አካባቢ ከፍተኛ የመሬት መንሸራተት ስላለ ተፈጥሯዊ ሁኔታውን ያገናዘበ ጥናት በመሥራት ግንባታውን ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
በዚህ ወቅት ከመነሻ እስከ 37 ኪሎ ሜትር ድረስ የተፋሰስና የአፈር ቆረጣ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ የጠጠር ሙሌት (ሰብቤዝ) እየተከናወነ ነው፤ በቅርቡም ወደ አስፋልት የመቀየር ሥራው መቀጠሉም ታውቋል፡፡ ሙሉ የሥራ መሣሪያ መቅረቡን የጠቀሱት ኢንጅነር ተስፋዬ አስፋልት ለማንጠፍ የሙከራና የላብራቶሪ ፍተሻ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከ37 እስከ 42 ኪሎሜትር የጎረቤላ ከተማን የሚያካልለው መንገድ እስካሁን አልተጀመረም፡፡ እንደ ቡድን መሪው ማብራሪያ የመንገዱን የአፈር ቆረጣ ለመጀመር በከተማው በርካታ ቤቶችን ማንሳት ይጠበቃል፡፡ የመብራት፣ የውኃና የቴሌኮምዩኒኬሽን መሰረተ ልማቶችን ለማንሳትም ሰፊ ጊዜ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ተቋራጩ የጊዜ ማራዘሚያ ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቀዋል፡፡
ባለስልጣኑ ለጥያቄው ውሳኔ ለመስጠት እያጤነ መሆኑን ያነሱት ኢንጅነር ተስፋዬ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ መጠናቀቅ በሁኔታዎች የሚወሰን መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሥራው በፍጥነት ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ወረዳው ፈጥኖ ተለዋጭ ቦታ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፣ ከሕዝቡም ከፍተኛ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ