
‹‹ለሀገራዊ ሰላም እና ልማት የአማራ ክልል መንግሥት እና ህዝብ ግንባር ቀደም ሆኖ ይቀጥላል›› ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር
ባሕር ዳር፡ የካቲት 01/2013 ዓ.ም (አብመድ) ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ኢ-ፍትሐዊ የምጣኔ ሃብት እና መሰረተ ልማት መስፋፋት ምክንያት ባላቸው ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ፀጋዎች ልክ አልተጠቀሙም ከሚባሉት ክልሎች መካከል አንዱ የአማራ ክልል ነው፡፡
በቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርክ እና በፊቬላ የተጣራ ምግብ ዘይት ኮምፕሌክስ ምረቃ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ የቴክኒዮሎጂ ሽግግርን የሚያፋጥን የፋይናንስ እጥረት እና የግል ባለሃብቱ በሚፈልገው መጠን እና መስክ መዋዕለ ንዋዩን አፍስሶ ማልማት የማይችልበት ጊዜ ትውስታ ቅርብ ነበር ብለዋል፡፡
የዛሬዎቹ ሁለት ግዙፍ ፍብሪካዎች መጠናቀቅ እና ወደስራ መግባት ከነውስንነቶቹም ቢሆን የኢትዮጵያን ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ እና ብልጽግና ለማረጋገጥ የምናደርገው ጥረት ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡
የግል ባለሃብቱ የመልማት እና የማልማት ፍላጎት በነበረው የመንግሥት የስርዓት ድክመት እግር ከወርች ታስሮ እንደነበር ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግል ባለሃብቱ ከመንግሥት ጋር ባደረገው ጤናማ ግንኙነት ተስፋ ሰጭ ምልክቶች እየታዩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጭ የተደረገበት እና የሃገሪቱን የምግብ ዘይት ፍላጎት እጥረት ስር ነቀል በሆነ መንገድ የሚፈታው ፊቬላ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ ማሳያ ሆኗል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው፡፡
የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርክ እና ፊቬላ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ መመረቃቸው በራሱ ለክልሉ ግብ አይደለም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ የተመረቁትን ፍብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ወደስራ እንዲገቡ የሚስተዋለውን የኃይል እጥረት ለመቅረፍ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡
ፍብሪካዎቹ የሀገር ውስጥ እና የውጭ የኢንዱስትሪ ፍላጎትን በመሳብ፣ የውጭ ምንዛሬ ችግርን ለማቃለል ካላቸው ፋይዳ በዘለለ የክልሉን አርሶ አደር ትርፍ አምራችነት እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ የሚኖራቸው ሚና የጎላ ነው ተብሏል፡፡
የክልሉ መንግሥት አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል ክልሉ ለባለሃብቶች ምቹ የሥራ አካባቢ እንዲሆን እንሰራለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ‹‹ለሀገራዊ ሰላም እና ልማት የአማራ ክልል መንግሥት እና ህዝብ ግንባር ቀደም ሆኖ ይቀጥላል›› ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ