“አይዞሽ አሞራ አይዞሽ ጭልፊት ፣ ቃኘው ሻለቃ አልፏል ከፊት”

512
“አይዞሽ አሞራ አይዞሽ ጭልፊት
ቃኘው ሻለቃ አልፏል ከፊት”
ባሕር ዳር ፡ የካቲት 01/2013 ዓ.ም (አብመድ)
ዓለም ተደመመ፣ ጠላትም ገረመው፣ ጀግንነታቸው ወደር የሌለውን አየና አደነቀ። ተደነቀ ። በዝናቸው ተጨነቀ። በግርማቸው ተሸማቀቀ። በሞገዳቸው ወደ ኋላ ራቀ። በጥይታቸው በየተራ ወደቀ። የእነርሱን ፊት፣ የተኮሱትን ጥይት ችሎ የሚቆም አልገኝ አለ። ከፍ ባለ ተራራ፣ ከፍ ባለ የዓለም ታሪክ ከፍ አድርገው ሰንደቁን ሰቀሉት። ኢትዮጵያ ትጠየቅ ጀግና ወላድ የመሆኗ ሚስጥር ምን እንደሆነ። አዎን ትጠየቅ መሸነፍ ለእርሷ አለመሠራቱ ምን እንደሆነ።
መታደሉ ለወዳጃቸው፣ ልክ የለውም ፍቅራቸው፣ አይታጠፍም ቃላቸው፣ አይመለስም ክንዳቸው፣ አይናወጥም እምነታቸው። ወዮሎት ለጠላት፣ አይመሩትም የተወለደበትን ቀን ቢረግማት፣ የወጣባትን ማሕፀን ዳግም ቢመኛት፣ ከቶም አያመልጥም ምድርን ለመደበቂያ ቢያስሳት። ምድር ብትታሰስ፣ ጀግና ሁሉ ቢጠራ በኢትዮጵያውያን ልክ ያለ አይመስልም።
እቴጌ ዘውዲቱ በግርማና በሞገስ በዙፋኑ ላይ ተቀምጠዋል። መኳንንቱና መሳፍንቱ ሠራዊቱና ሊቃውንቱ ሁሉ በፈቃደ እግዚአብሔር የነገሱትን እመቤትና የሚወዳትን ሀገር ያገለግል ነበር። ሀገራቸውን በቅንነት ከሚያገለግሉ ኢትዮጵያውያን ሹማምንት የጎጃሙ ባላበት
ቀኝ አዝማች መሠሉ ካሳ አንዱ ነበሩ። በይልማና ዴንሳን ይኖሩ ነበር። ባለቤታቸው በትሃ ወንዱ ይባላሉ። ቤታቸው በደስታ የተመላ፣ ጮማና ፍትፍት የሚወርድበት፣ ማርና ወተት የሚቀዳበት ነው። 1919 ዓ.ም ደረሰ። ቀኝ አዝማች መሠሉና እሜቴ በትሃ ለመልካሙ ትዳራቸው ማድመቂያ የልጅ ስጦታ ተሠጣቸው። መጪው ዘመን አስቀድሞ የታወቃቸው ይመስላል አራጋው ሲሉ ስም አወጡለት። በስሙ ያደገው ብላቴና ለክብር ተዋጋ። ድንበር ተሻግሮ ሀገር አረጋ።
ከመኳንንትና ከመሳፍንት መንደር የተወለዱት የመኳንንቱ ልጅ በሞገስ አደጉ። በፍቅር ኖሩ። ሲጠማቸው ማርና ወተት እየጠጡ፣ ሲርባቸው ፍትፍት እየበሉ በክብር አደጉ። 12 ዓመታት ሲሆናቸው ወላጆቻቸው ቤት ወጥተው ወደ አጎታቸው ቤት ገቡ። አጎታቸው ፊታውራሪ ታደለ ትርፌ ይባላሉ። ጀግንነታቸው የታወቀ ልባቸው በሀገር ፍቅር የተመላ ነበሩ። ጥቂት በጥቂት አደጉ። ተኩስ ተማሩ። ግብርናውንም ተካኑበት። ለአቅመ አዳም ደረሱ። አቻቸው ተፈልጋ በክብርና በሞገስ፣ በታላቅ ደስታ፣ በእልልታና በሆታ ተዳሩ። ልጆችም ወለዱ። አራጋው ከትዳር በስተማዶ ለሀገር መዋደቅ የልባቸው ምኞት ነበርና ሠራዊት መሆን ወደዱ። ትዳራቸውን ትተው የክብር ዘበኛ ሆነው ተቀጠሩ።
የዚያኔው የቀትር እሳት የዛሬው አዛውንት የሠላም አምባሳደር በኩረ ምዕመናን አራጋው መሠሉ ያን ጊዜ ሲያስታውሱት “በ23 ዓመቴ ወደኮሪያ ዘምቻለሁ። ሀገሬ ኢትዮጵያን እወዳታለሁ። ለምን ቢባል ያለ ሀገር ሰው ምንም ሊሆን አይችልም። ወደ ጦር ሜዳ ሄጄ ያሰብኩትን አሳክቻለሁ። ማንም አላስገደደኝም ለሀገሬ የነበረኝ ፍቅር ነው ወደ ጦርነት እንድገባ ያደረገኝ፣ ወንድሞቼና አጎቶቼ ለሀገራቸው የተዋደቁ ጀግኖች ነበሩ። ከእነርሱ ጋር ነው ያደኩት። የእነርሱን ጀግንነት ተቀብዬ ወደ ኮሪያ ዘምቻለሁ” ነበር ያሉት።
ያ ዘመን የሀገርን ዳር ድንበር ከመጠበቅ በዘለለ በቀውስ ውስጥ የነበሩ ሀገራትን የማረጋጋት ድርብ ኃላፊነት ነበር። በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የምትመራው ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም መጠበቅ ዘብ ከቆሙ ሀገራት መካከል ከቀዳሚዎቹ ነበረች። ሰላም ወደተናጋበት፣ ዙፋን ወደ ተደፈረበት ሀገር ሁሉ ልጆቿን እየላከች በአስፈሪው ግርማዋ ሰላምን ትመልስ ነበር። የሠላም አምባሳደር በኩረ ምዕመናን አራጋው ለሠላም ከተላኩ ጀግና ኢትዮጵያውያን መካከል አንደኛው ናቸው።
በሀገራቸው ወታደራዊ ስልጠና ሰለጠኑ። ለጦርነትም ዝግጁ ሆኑ።
“በኮሪያ በዘመትን ጊዜ <እልም አለ ባቡሩ እልም አለ ባቡሩ፣ ወጣቱን ይዞ በሙሉ> እየተባልን ሄድን።
ቀይ ባሕር ገባን። ወደዚያም ሄድን። ከዚያም ደረስን። እንደደረስን የአሜሪካ ጦር መሪ አነዚህማ ደካሞች አይደሉ ከባድ መሳሪያ አያጋላብጡም። በጦርነት አይራመዱም አለን። እንግዲያስ እናሳይ አልን። ትርኢት አሳዬን። አንደኛ ሆን። ወደጦርነት የመግቢያ ጊዜያችን ደረሰ። የጠላት ጦር የሰፈረበት እንድ አስፈሪ ተራራ አለ። ያን ቦታ ከጠላት ለማስለቀቅ ብዙ ሠራዊት አልቆበታል።
የኢትዮጵያ ጦር ተራ ደረሰ። ወደጦርነቱ ገባ። በ24 ሰዓታት ውስጥ ተራራውን ተቆጣጥረን። ወዲያው ተራራውን ይዘነዋል ብለን ተናገርን። የአሜሪካው የጦር መሪ < እንኳን እናንተ እኛም አልያዝነው ለምን ትዋሻላችሁ አለን> መጥተህ እይ አልነው። በሄሊኮፕተር መጥቶ አዬው። በተራራው ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባንዴራ እየተውለበለበ አየው። አደነቀ። አመሰገነ። ለሜጄር ጄኔራል አይዘናውር ነገረው። ሜጄር ጄኔራል አይዘናውር የኢትዮጵያን ሠራዊት ማዬት አለብኝ ብሎ መጣ። ባየው ሁሉ ተገረመ” ነው ያሉት አራጋው ያን ጊዜ ሲያስታውሱት።
“ኢትዮጵያን ከመውጋት የኢትዮጵያን ጠላት ከኢትዮጵያ ጋር ሆኖ መውጋት ይሻላል” እያሉ ያደንቁ እንደነበርም ነግረውኛል። የቃኘው ሺህ አለቃ ግርማው አስፈሪ ነበርና
“አይዞሽ አሞራ አይዞህ ጭልፊት፣ ቃኘው ሺህ አለቃ አልፏል ከፊት” እየተባለ ይገጠምላቸው እንደነበርም ነግረውኛል።
የደረሱበት ጠላት ሁሉ ይደነብራል፣ ይሸበራል። የሚሆን አይደለም የተባለው ምሽግ ሁሉ ይሰባበራል። በሶስተኛ አባ ቃኘው ሺህ አለቃ የዘመቱት የሠላም አምባሳደር በኩረ ምዕመናን አራጋው ከኢትዮጵያ እስከ ኮሪያ ተመልሰውም በኢትዮጵያ አያሌ ጀብዶችን ፈፅመዋል። በኮሪያ ዘመቻ ምን ነበር ? “የእኛ ባንዲራ ብቻዋን ተወልለበለበች። አንድም ምርኮኛ አልነበረም” ነበር ያሉት። ኢትዮጵያውያን እንኳን በቁማቸው እጅ መስጠት ይቅርና ሬሳቸውን አሳልፈው ለሰው አይሰጡም። መሸነፍና መማረክ ለኢትዮጵያውያን የተፈጠረና የተገባ አይደለም። ለዚህ ደግሞ የአቃኘው ምልምል አራጋው ምስክር ናቸው።
እኒህ ጀግና የኮሪያ ግዳጃቸውን በአንድ ዓመት ከስምንት ወራት አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ተመለሡ። ሀገራቸውን በቅንነት ማገልገል ቀጠሉ። ሌላ ግዳጅ መጣ። ከሀገራቸው ወጥተው ወደኮንጎ ኪኒሻሳ ለሰላም ማስከበር ሄዱ። የኮሪያውን ገድል በኮንጎም ደገሙት። ዓለም በድጋሜ ተደነቀ። ያንም አጠናቀቁ። ወደ ሀገራቸውም ተመለሱ። ሶማሊያም ኢትዮጵያን ወረረች። ጦራቸውን መዘው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ዘመቱ።
ማሸነፋቸው ከመግጠማቸው አስቀድሞ የሚታወቀው ኢትዮጵያውያን የሶማሊያን ወራሪ እንዳልነበር አደረጉት። ቀጥተው አሳፈሩት። ማርከው አንገቱን አስደፉት። ገድለው ከአፈር አዋሃዱት። የአባ ቃኘው ምልምል አራጋው የሀገራቸው ውለታ በዚህ አላበቃም። በኢትዮጵያ ዳር ድንበር የሚነሳውን ጠላት አይቀጡ ቅጣት እየቀጡ ጀብድን ፈፀሙ። አጀብ የሚያሰኝ ጀግንነት ፈፅመው ከሚወዱት ሠራዊት ወጡ።
ዳግም ትዳር ቀለሱ። ባለቤታቸው ወይዘሮ ዝይን መኮንን ይባላሉ። ታሪካቸውን ለመስማት የታደልነው ከዝይን ጋር የተጋቡበትን 50ኛ ዓመት በባሕር ዳር በመኖሪያ ቤታቸው ሲያከብሩ አግኝተናቸው ነው። የአባ ቃኘው ምልምል ለክብር በጦር ሜዳ ዘማች፣ ጠላትን መካች፣ ለፍቅር ሟች ናቸው። ለዚያም ነው በእሳት በተፈተነው የውትድርና ሕይወታቸው ወጥተው 50 ዓመታትን በትዳር ያሰለፉት።
“የወንዶች መሪ ሕግ አስከባሪ
ጦር ሜደ ወርዶ ቦንብ አሽከርካሪ
በየሸለቆው ጠላት መንጣሪ
በደረሰበት ምሽግ ሠባሪ
ቀለህ ከማሪ እርሳስ አብራሪ” ተብሎላቸዋል።
እኒህ ታላቅ ሰው የተባበሩት መንግሥታት የወርቅ ሜዳሊያ፣ የኮሪያ መንግሥት የታላቅ ጀግንነት ክብር የወርቅ ሜዳሊያ፣ የግርማዊ ቀደማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት የጅግንነት ክብር የወርቅ ሜዳሊያ፣ በኡጋንዳ የሠላም ማስከበር የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የብር ሜዳሊያ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቃል ኪደን መሠረታዊ ላበረከቱት የኮሪያ የውርቅ ዘንባባ ሜዳሊያ፣ የኮንጎ ኪኒሻሳ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለ ዘንባባ የክብር የነሃስ ሜዳሊያ፣ በድጋሜ ጎንደር ላይ በተካሄደ ስነ ስርዓት የኮንጎ የወርቅ ኒሻን እና ሌሎች ኃያሌ ሽልማቶችን ለክብራቸው ተቀብለዋል። ለሰላም ላበረከቱት አስተዋጽኦ የሰላም አምባሳደር ሲባሉ፣ በሃይማኖታቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ደግሞ በኩረ ምዕመናን የሚል ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል።
የሠላም አምባሰደር በኩረ ምዕመናን አራጋው የፍርድ ሸንጎ ሆነው ሕዝባቸውን በታማኝነት አገልግለዋል። የተጣላን በማስታረቅ፣ ሕዝብ በማዋደድም ይታወቃሉ። በበርካታ የልማት ሥራዎችን በመሥራትም እንዲሁ። ለሀገራቸው ቋሚ፣ ለሃይማኖታቸውም ቀናዒ ናቸው። የባሕርዳር ደብረ ፅዮን ሠላም አድርጊው ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያንን ኮሚቴ ሆነው አሰርተዋል።
50ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸውን ያከበሩት ታላቁ ሰው ከባለቤታቸው ጋር ስላሳለፉት ጊዜ ሲናገሩ “ነዝናዛ ሚስት ያለው ሰው ከሠው ለቅሶ አይሄድም ከቤትም ለቅሶ ነው። ጥሩ ሚስት ያለው ሰው ከሰው ሰርግ አይሄድም። ከቤቱም ሰርግ ነው። ከባለቤቴ ጋር በደስታ ነው የምኖረው። እወዳታለሁ ትወደኛለች” ነው ያሉት።
ታላቁ ሰው ያላቸውን ሁሉ ለሀገራቸውና ለሃይማኖታቸው ሰጡ። እግዚአብሔር ደግሞ እድሜ፣ ጤናና ፀጋውን ሰጣቸው። ወይዘሮ ዝይን ባለቤታቸውን “በፍቅርና በደስታ ነው የኖርነው፣ አክባሪ ናቸው፣ ያከብሩኛል፣ አከብራቸዋለሁ” ነው ያሉት። ጎረቤቶቻቸውም አይቻልም እንጂ ቢቻል ኖሮ እድሜ እንሰጣቸው ነበር ያሉን። ታላቁ ሰው ያመኑበትን ከመናገር ወደ ኋላ የማይሉ ስለመሆናቸውም ነግረውናል።
ሀገር ያለ ሽማግሌ ምንም ናት ያሉን ጎረቤቶቻቸው ዋርካው እንዳይወድቅ እየሰጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ሁለቱ ጥንዶች የጋራ አራት ልጆችን አፍርተዋል። ተጨማሪ የየራሳቸው ልጆችም አሏቸው። 31 ያክል የልጅ ልጆችንም ማዬታቸውን ታላቁ ሰው ነግረውናል። ልጆቻቸውንም ለቁም ነገር አብቅተዋል። ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ መቻቻል፣ በሀሳብ ልዩነት ማመን እና ደግነት ከወላጆቻቸው መውረሳቸውን ልጆቻቸው ነግረውናል። በመቻቻል የተመሰረተው ትዳራቸው 50 ዓመታትን በፍቅር ዘልቋል። ዛሬም አላረጀም። አዲስ ነው። በስስት ያስተያያል፣ በናፍቆት ያውላል። ዛሬም እንደ ቀደመው ከፊታቸው የፍቅር ፈገግታ አይጠፋም። ይልቁንም እየቆየ ውብ ሆኗል።
ለእኒህ ታላቅ ሰው የኮሪያ መንግሥትና ድርጅቶች ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ነግረውናል። ኢትዮጵያ መልካም ሀገር ናት፣ ብዙ የሚመኛት የሀብት ሀገር ናት፣ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ቦታዎች የሚደረገው ነገር ለኢትዮጵያ አይበጅም ነው ያሉት። ለኢትዮጵያ የፀና አንድነት እንደሚያስፈልግ ነው የመከሩት። “ኢትዮጵያ እናት ናት። አጥብታ ያሳደገች። ካለ ሀገር መኖር የለም። ኢትዮጵያ ጥሩ ሲሳይ ያለባት እንጀራ የምትሰጥ ናት። በፍቅርና በአንድነት ሆኖ ሀገር መንከባከብ ይገባል” ነው ያሉት።
በፍቅር የተሰራች ጎጆ መልካምነት ተጠልሎባት ዓመታትን ተሻገረች። መልካም ፍሬም ተገኘባት። የፍቅር ቤት አይፍርስም። እውነተኛ ፍቅር በጊዜ ብዛት አይለወጥም። በእድሜ መግፋት አይደበዝዝም። እያደር እያሳሳ ይሄዳል እንጂ። የእነርሱን ፍቅር፣ ክብር፣ ታሪክና ዘመን አብዝቼ ተመኘኋት። አገኛቸው ዘንድ ተማፀንኩ። በፍቅርም በጦርም መምህር ናችሁና ዘለግ ያለ እድሜ ተመኘሁ። በፍቅር ቤታችሁ ውስጥ የፍቅር አምላክ ይገባ። ሌሎችም ከእናንተ ጥልቅ የፍቅር ባሕር ይጠጡ።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“መንግሥት የኅብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሠራ ይገኛል” የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀለመወርቅ ምህረቴ
Next articleበኩር ጋዜጣ የካቲት 01/2013 ዓ/ም ዕትም