
“መንግሥት የኅብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሠራ ይገኛል” የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀለመወርቅ ምህረቴ
ባሕር ዳር፡ ጥር 30/2013 ዓ.ም (አብመድ) የደቡብ ጎንደር ዞን እብናት ከተማ የከተማ አስተዳደርነት ጥያቄ መልስ በማግኘቱ በከተማዋ ሕዝባዊ መድረክ ተካሂዷል፡፡
በአማራ ክልል ለከተማ አስተዳደርነት ጥያቄ ሲያቀርቡ ከነበሩት ከተሞች አንዷ የሆነችው እብናት የከተማ አስተዳደርነት ጥያቄ መልስ አግኝታለች፡፡ ነዋሪዎችም ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡
ከነዋሪዎች መካከል ሼህ ሃሰን ሲራጅ እንደተናገሩት የሕዝቡ ሲያነሳ የነበረውን የከተማ አስተዳደርነት ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎችም የሕዝቡ ጥያቄዎች ማዕከል ያደረገ ሥራ እንዲያከናውኑ ጠይቀዋል፡፡ በተለይም በመሰረተ ልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ የሚገባ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ የሚጠይቀውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የእብናት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉጌታ ይማም እንደገለፁት የእብናት ወረዳ በ1902 ዓ.ም የተቆረቆረችና የ111 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረች ከተማ መሆኗን ተናግረዋል፡፡ በዕድሜዋ ልክ የምትፈልገውን ዕድገት ማስመዝገብ ያልቻለችው እብናት ብዙ የመስረተ ልማት ጥያቄዎች ቢኖሩም የከተማ አስተዳደርነት ጥያቄ መልስ መገኘቱ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት በቀጣይም ለከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊ መሰረተ ልማት ለማሟላት ተገቢውን ትኩረት ስጥቶ እንዲያግዛቸው ጠይቀዋል፡፡
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ቀለመወርቅ ምህረቴ “እብናት ወረዳ በዞኑ የከተማ አስተዳደርነት ጥያቄ መልስ ካገኙ የወረዳ ከተሞች አንዷ ናት፤ ይህም መንግሥት የኅብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሠራ እንደሚገኝ ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ በአዲስ የተመደቡ የሥራ ኃላፊዎችም የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመቼውም በላይ በትጋት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ከከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ጎን በመሆን ለዘላቂ ዕድገት ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ንጉስ ድረስ – ከእብናት
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ