
ቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ዛሬ ይመረቃል፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 30/2013 ዓ.ም (አብመድ) በፌደራል ደረጃ ሞዴል ተብለው ከተመረጡት አራት የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች መካከል አንዱ የሆነው ቡሬ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ግንባታው የተጀመረው በ2010 ዓ.ም ነበር፡፡
ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 1 ሺኅ ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈው የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ዛሬ የሚመረቀው የመጀመሪያው ምዕራፍ በ260 ሄክታር ላይ ያረፈ ነው፡፡
እስካሁን ባለው የግንባታ ሂደት 4 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ወጭ የተደረገበት ይህ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በ100 ኪሎ ሜትር ራዲየስ 7 መጋቢ የገጠር የሽግግር ኢንዱስትሪያል ፓርኮችን ያቀፈ ነው፡፡ ሞጣን ጨምሮ ከአማኑኤል እስከ ፍኖተ ሰላም፣ ከዳንግላ እስከ መርዓዊ፣ ከእንጅባራ እስከ ቻግኒ የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ መጋቢ ማዕከላት ሆነው ያገለግላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በቡሬ ኢንዱስትሪያል ፓርክ 9 ኢንዱስትሪዎች እና በሦስት ባለሃብቶች አራት ፕሮጀክቶች ወደሥራ ገብተዋል፡፡ ሪች ላንድ ባዮ ኬሚካል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በ900 ሚሊየን ብር ወደስራ ገብቷል፡፡ በሙሉ አቅሙ መስራት ሲጀምርም 66 ሚሊየን ዶላር ዓመታዊ ገቢ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባሕር ዳር አግሮ ፕሮሰሲንግ እና ዮሴፍ ነጋ ቲማቲም ማቀነባበሪያ ፍብሪካ ወደሥራ መግባታቸውን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዛሬ ለምረቃ የሚበቃው የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ማኅበራዊ ተቋማትን፣ የመብራት፣ መንገድ፣ ቴሌ ኮም እና ውኃ መሰረተ ልማት ግንባታዎችን፣ እሳት አደጋ መከላከያ፣ የገበያ ማዕከል፣ የአስተዳደር ህንፃዎችን፣ የጉምሩክና ጥበቃ ማዕከላት እና የስፖርት ማዘውትሪያ ሜዳዎች ተገንብተውለታል፡፡
የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ከፌደራል እና ክልል የተውጣጡ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ይመረቃል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከቡሬ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ