ኢትዮጵያ የቁም እንስሳትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የምታገኘው ዓመታዊ ገቢ ማሽቆልቆሉን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

289
ኢትዮጵያ የቁም እንስሳትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የምታገኘው ዓመታዊ ገቢ ማሽቆልቆሉን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ዓመታዊ ገቢ ከ200 ሚሊዮን ዶላር ወደ 50 ሚሊዮን ዶላር አሽቆልቁሏል፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ 59 ሚሊዮን የቀንድ ከብት፣ 60 ሚሊዮን ፍየልና በግ፣ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ግመል አላት፡፡ ይህም በቁም እንስሳት ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚ፣ ከዓለም ደግሞ ዘጠነኛ ደረጃን እንድትይዝ አድርጓታል፡፡
ኢትዮጵያ የቁም እንስሳትን ለውጪ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ ገቢ ያገኘችው በ2004 ዓ.ም ነበር፡፡ በጊዜው ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ አግኝታ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ ከፍተኛ ቅናሽ ማሳየቱን ነው የኢፌዴሪ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያስታወቀው፡፡
በቅርብ ጊዜያት ከቁም እንስሳትና ከእንስሳት ተዋዕጾ ግብይት የሚገኘው ዓመታዊ ገቢ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በታች መሆኑም ታውቋል፡፡ ለዚህም ሕገወጥ የቁም እንስሳት ንግድ መስፋፋት፣ በዘርፉ የባለሀብቶች ተሳትፎ አናሳ መሆን፣ ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ አለመኖር፣ የእንስሳት ጤና አገልግሎት ዝቅተኛ መሆን፣ በእንስሳት ውጤት ላይ ዕሴት ጨምሮ ለውጪ ገበያ አለማቅረብና ተያያዥ ችግሮች ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው ተብሏል። በተለይ ክልሎች በዘርፉ ሕግ የማስከበር ድክመት እንዳለባቸው በሚኒስቴሩ የቁም እንስሳት ግብይት ማስፋፊያ ባለሙያ አበበ ታደሰ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ አበበ መረጃ ያደጉ ሀገራት የቁም እንስሳትን በከፍተኛ ደረጃ ጥራታቸውን ጠብቀው ለውጪ ገበያ ያቀርባሉ፤ በእንስሳት ተዋዕጾ ላይ እሴት በመጨመርም ከፍተኛ ገቢ ያገኛሉ፤ ከነችግሩም ቢሆን በኢትዮጵያ በብዛት የተለመደው እንስሳትን በቁም ለውጪ ገበያ ማቅረብ ነው፤ ይህም ቢሆን ዘመናዊ የእንስሳት ርባታ ባለመኖሩ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ አመርቂ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የቁም እንስሳትን ወደ ጂቡቲ፣ ሶማሌላንድ፣ የመንና አረብ ሀገራት ትልካለች፡፡ ሀገራቱ ደግሞ እሴት ጨምረው እንደገና ለውጪ ገበያ ያቀርባሉ፤ከፍተኛ ገቢ እንደሚያገኙበትም አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተወሰነ ደረጃ የእርድ ስጋ ለውጪ ገበያ ብታቀርብም እሴት ከመጨመር አንጻር መሠረታዊ ክፍተት መኖሩን አስታውቀዋል፡፡
በአማራ ክልል የተሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች ቢኖሩም በዘመናዊ መንገድ አርብቶ ለመጠቀም ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አቶ አበበ ጠቅሰዋል፡፡
ነባር የእንስሳት ርባታ ማዕከላት ጭምር የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው አመላክተዋል፡፡
በሱዳን ድንበር በኩል ካሁን ቀደም ከፍተኛ ሕገወጥ ንግድና የቁም እንስሳት ዝውውር መኖሩን አንስተዋል፡፡ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማትም ይህንኑ አረጋግጧል፡፡በቢሮው የእንስሳትና እንስሳት ተዋዕጾ ግብይት ዳይሬክተር አቶ አንተነህ አለሙ እንዳሉት በተያዘው በጀት ዓመት 5 ሺህ ገደማ የቁም እንስሳት በሕገወጥ መልኩ ሲዘዋወሩ ተይዟል፡፡ በዚህም ልዩ ልዩ ውሳኔዎች መሰጠቱን አቶ አንተነህ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ተደራሽ ባልሆኑ አካባቢዎች ችግሩ እንደቀጠለ ነው ብለዋል፡፡
በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት 14 ተቋማትን ያካተተ ቡድን ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ቡድኑ በክልሉ ርእሰ መሥተዳድር የሚመራ ሲሆን ተቀናጅቶ በመሥራት በኩል የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝ ነው ያስታወቁት፡፡
የሀገሪቱን የእንስሳት ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም የግብይት ማዕከላትንና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል አቶ አበበ፡፡ የሚሌ ዓለም አቀፍ ኳራንቲን በዚህ ዘርፍ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ይህ ኳራንቲን በአንድ ዙር ከ40 ሺህ እስከ 50 ሺህ እንስሳትን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን ለግል ባለሀብት ለማስተላለፍ ጨረታ መውጣቱን አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡ ይህም የሀገሪቱን የእንስሳት ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ይረዳል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleተመራቂ ተማሪዎች የሕይወት ዘይቤያቸው አንድነት እንዲሆን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ጠየቁ፡፡
Next articleብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት 420 የህወሃት ከፍተኛ የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮችና 682 በወንጀል ድርጊት የተሳተፉ የጁንታው አባላት ላይ መረጃ በማሰባሰብ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።