
ተመራቂ ተማሪዎች የሕይወት ዘይቤያቸው አንድነት እንዲሆን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ጠየቁ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አገኘሁ ተሻገር በባሕርዳር ዪኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምረቃ ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ለክልሉ እንደ ዓይን ብሌን የሚታይ ግዙፍ የዕውቀት ማዕከል ነው ብለዋል፡፡
ተመራቂዎች ዓለምን በአስቸገራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የነበረውን ፈተና አልፈው በመመረቃቸው ታሪካዊ ተመራቂዎች ናቸውም ብለዋል፡፡
በሀገራችን የታዬውን የለውጥ ወጋገን ለማጨለም የሚጥሩ ኃይሎች፣ የሕዝባችን ህልውናና የሀገሪቱን አንድነት እየተፈታተኑት እንደሚገኙም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል፡፡
የትህነግ ኃይልና መሰል የጥፋት ኃይሎች እንዲሁም የውጭ ጠላቶች በቅንጅት በዜጎችቻን ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ አሰቃቂ ግድያ፣ ማፈናቀልና ንብረት ማውደም አድርሰዋል፤ በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ አልፋችሁ በመመረቃችሁ ዕድለኞች ናችሁ ብለዋል ርዕሰ መስተዳደሩ፡፡
የሀገሪቱን የለውጥ ጉዞ፣ ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋት፣ የሕግ የበላይነት፣ ሉዓላዊነት፣ አንድነትና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በሰከነ መንገድ ለማራማድ ከፍተኛ ተስፋ የተጣለባችሁ ናችሁም ብለዋል፡፡
ተመራቂ ተማሪዎች ሀገርና ቤተሰብ የጣለባቸውን አደራ በአግባቡ እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡ ራሳቸውን ለሁለንተናዊ የህይወት ትግል እንዲያዘጋጁም ነው ያሳሰቡት፡፡ በመንግሥት ጥገኝነት የተመሰረተ ምጣኔ ሀብት ዘላቂ ሊሆን እንደማይችል ከሀገራት ተሞክሮ ተመልክተናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገሬ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን ለሀገሬ ምን አደረኩላት የሚል የመንፈስ ቁርጠኝነት፣ የሙያ ግዴታና የዜግነት ግዴታችሁን መወጣት ይገባል፤ ሀገሪቱም ብዙ ነገር ትጠብቅባችኋለች ብለዋል፡፡
በሸመቱት እውቀትና ክህሎት በቆይታቸው ያደበሩትን የአብሮነት እሴትና መቻቻል በየተሰማሩበት የሙያ መስክና አካባቢ በላቀ ሁኔታ እንደሚተገብሩትም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን አንድነት አክብረው እንዲኖሩና የሕይወት ዘይቤያችሁ አንድነት እንዲሆንም አደራ ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ