
“የ125ኛው የአድዋ ድል በዓል የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ባሕር ዳር፡ ጥር 28/2013 ዓ.ም (አብመድ) የ125ኛው የአድዋ ድል በዓል የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከ125 ዓመታት በፊት በአፍሪካ ሰማይ ስር በኢትዮጵያ ምድር የተገኘው የአድዋ ድል መልከ ብዙ ነው።
ታላቁ የአድዋ ድል ዘመናዊት ኢትዮጵያን ከጥንታዊ ታሪኳ ጋር ያዋደደ፤ የጥንቶቹን አባቶቻችን ጀግንነትና ለሀገር ያላቸውን ፍቅር ያስመሰከረ፣ የነጻነት አይበገሬነት ወኔን ያሳየ፣ የሕዝቦች አንድነት ህያው ማሳያ ታሪካዊ ሁነት ነው።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች እንድትታወቅ፣ ዝናዋ እንዲናኝና እንድትከበር ምክንያት ሆኗል፤ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት እርሾ ሆኗል።
አድዋ በሌሎች ሀገሮች ሕዝቦች የነጻነት ትግል ተምሳሌት ሆኖ በተለይም የጥቁር ዓለም ሕዝቦችን ያነሳሳ፣ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲቀነቀን ያስቻለ ድል ነው።በዚህም በአፍሮ አሜሪካዊያንና በአፍሪካዊያን እንዲቀነቀንና እንዲያብብ በማድረግ ለፓን-አፍሪካዊነት ትንሳኤ መሰረት ጥሏል።
የአድዋ ድል ቅኝ ገዥዎችን የአገዛዝ ፖሊሲያቸውን ጭምር እንዲመረምሩ ያደረጋቸውና
ኢትዮጵያ ሉዓላዊት ሀገር መሆኗ እንዲረጋገጥ ያስቻለ ነው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አድዋ ኢትዮጵያ በሀገሮች የምትታወቅበት፣ የምትከበርበትና በሀገሮች ለተወከሉ ዲፕሎማቶችና ዜጎች የኩራት አክሊል እንደሆነ ይገልጻሉ።
የአድዋ ድልን 125ኛ በዓል በድምቀት ለማክበር እየተሠራ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ ከበዓሉ አከባበር ኮሚቴ አባላት አንዱ ሆኖ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ