
ኢትዮጵያ ውስጥ በአበባ እርሻ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የ2 ቢሊዮን ፓውንድ ድጋፍ መዘጋጀቱን የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ገለጸ።
ባሕር ዳር ፡ ጥር 27/2013 ዓ.ም (አብመድ) በዩናትድ ኪንግደም የኢትዮጵያን የአበባ ምርት የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጭ እድሎችን ለማስተዋወቅ በ’ቨርቹዋል’ የታገዘ የኢኮኖሚ ውይይት ተደርጓል።
ውይይቱ የተካሄደው በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተባባሪነት ነው። መድረኩ በሀገሪቱ የሚገኙ የአበባ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያለውን እድል ተገንዝበው መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈስሱ የሚያበረታታ መሆኑን በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ተናግረዋል ፡፡ አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ለውጭ ኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን ገልጸዋል።
ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እየተላከ ያለው የአበባ ምርት መጠን ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መሆኑንም አመላክተዋል። አዳዲስ የኢንቨስትመንትና የንግድ እድሎችን በማስፋትና የውጪ ገበያውን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአበባ ምርትን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከአፍሪካ ሁለተኛ እንደሆነች የግብርና ሚንስትር ዴኤታ ወንዳለ ሀብታሙ ገልጸዋል። ለዘርፉ ምቹ ሥነ ምህዳር፣ ለም መሬት፣ የመስኖ አማራጭና አዳዲስ የቀረጥ ነጻ ማበረታቻ መኖሩንም አስረድተዋል፡፡ የአውሮፓ ባለሃብቶች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአማራ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ጌታሁን መኮንን በርካታ የዩናይትድ ኪንግደም ኩባንያዎች በክልሉ የአበባ ምርት መሠማራታቸውን አስታውቀዋል። በኩባንያዎቹ አማካኝነት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የአበባ ምርት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑን ተናግረዋል። በክልሉ ዘርፉን ይበልጥ ማሳደግ የሚችል ተጨማሪ እድል መኖሩንም አብራርተዋል።
በቂ መሬት፣ የውኃ ሀብት እና የሰው ሃይል መኖሩን በመግለፅም አዳዲስ የታክስ ማበረታቻዎች እንደተዘጋጁም አንስተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ዶክተር በይሳ በዳዳም በተመሳሳይ በክልሉ ለአበባ እርሻ የሚሆን ምቹ ሁኔታ መኖሩን አብራርተዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንስን የኢትዮጵያ ልዩ የንግድ መልእክተኛ ሎርድ ቤትስ መንግሥታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ለዘመናት የዘለቀ ግንኙነት እንዳለው ተናግረዋል፣ ወደፊት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ላላቸው የሀገሪቱ ባለሃብቶች የ2 ቢሊዮን ፓውንድ ድጋፍ መዘጋጀቱንም አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ከፍተኛ እምቅ ሀብት ያላት ሀገር መሆኗን የገለጹት ደግሞ የቀድሞው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ልዩ የንግድ መልእክተኛ ጀረሚ ላፍሮይ ናቸው። ወደፊት የዓለም ሕዝብ ተስፋ ግብርና እንደሚሆን የጠቀሱት ጀርሚ ላፍሮይ ኢትዮጵያ ተመራጭ ሀገር መሆኗን መስክረዋል።
በተለይ በአበባ እረሻ ዘርፉ ሰፊ እድል መኖሩን በጥቀስ ባለሀብቶች ዕድሉን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
በለንደን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተወካይ ሚካኤል ዮሐንስ የአበባ ምርትን ወደ አውሮፓ ለመላክ አስተማማኝ አቅም መገንባቱን ገልፀዋል፡፡ በውይይቱ ከ50 በላይ የዩናይትድ ኪንግደምና የአውሮፓ አበባ አምራች ባለሀብቶች፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ልምዳቸውን አካፍለዋል። መረጃውን ያድሰን በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ