በኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ወደ ምርት ያልገቡ ፋብሪካዎችን ሥራ ለማስጀመር 9 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እንደተመደበ ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡

220
በኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ወደ ምርት ያልገቡ ፋብሪካዎችን ሥራ ለማስጀመር 9 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እንደተመደበ ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 26/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ግንባታቸው ተጠናቅቆ በኤሌክትሪክ ኃይል ችግር ምክንያት ሥራ ያልጀመሩ 24 ፋብሪካዎች መኖራቸውን የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የደብረብርሃን ከተማ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እየጨመረ ይገኛል፡፡ አካባቢው ያለው ምቹ የሰላም ሁኔታ፣ የአየር ፀባይ፣ በመንግሥት ተቋማት ፈጣን አገልግሎት አሰጣጥ፣ ሰፊ የኢንቨስመንት አማራጭ እንዲሁም በቂ የሰው ኃይል መኖር ለደብረብርሃን ከተማ ኢንቨስትመንት መነቃቃት ምክንያት ናቸው፡፡
የከተማዋ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ብርሃን ገብረሕይወት እንዳብራሩት በከተማዋ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ኢንዱስትሪዎች በአምራች ዘርፉ የተሠማሩና ዕርስ በዕርሳቸው ተመጋጋቢ ናቸው፡፡ ይህም ከውጪ ሀገር የሚገቡ ምርቶችን በመተካት የምንዛሬ እጥረትን ይቀንሳሉ፡፡ በ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ለቀረቡ 136 የተለያዩ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት በአምራች ዘርፉ ለመሰማራት ጥያቄ ያቀረቡ ናቸው እንደ ኀላፊው ማብራሪያ፡፡
በሌላ በኩል ከፍተኛ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችሉ ኢንዱስትሪዎች ሙሉ ግንባታቸው ቢጠናቀቅም ወደ ምርት አልገቡም፡፡ አቶ ብርሃን እንዳሉት 24 ፋብሪካዎች ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ማሽን ቢገጥሙም ፈጥነው ወደ ሥራ አልገቡም፡፡ ከ10 ሺህ በላይ የሥራ እድል መፍጠር የሚችሉት ፋብሪካዎች ሥራ ያልጀመሩት ከሰብስቴሽን ወደ ኢንዱስትሪ መንደሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መሥመር ባለመዘርጋቱ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት የክልሉ መንግሥት 9 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በመመደቡ ችግሩ በአጭር ጊዜ እንደሚፈታም አስታውቀዋል፡፡ በኢንቨስትመንት የተሠማሩ ባለሃብቶች በዘርፉ የሚስተዋሉ የመሠረተ ልማት ችግሮችን በመፍታት መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት እያገዙ መሆኑም ተመላክቷል፡፡ ወደ ከተማ አስተዳደሩ የሚቀርቡ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችን በቀላሉ ለማስተናገድ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ኀላፊው ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት በሁሉም ኢንዱስትሪ ክላስተሮች 5 ሺህ 503 ሄክታር መሬት መለየቱን አመላክተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleራስ ሚካኤል “አባ ሻንቆ”
Next articleኢትዮጵያ ውስጥ በአበባ እርሻ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የ2 ቢሊዮን ፓውንድ ድጋፍ መዘጋጀቱን የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ገለጸ።