ራስ ሚካኤል “አባ ሻንቆ”

2550
ራስ ሚካኤል “አባ ሻንቆ”
ባሕር ዳር ፡ ጥር 27/2013 ዓ.ም (አብመድ) ራስ ሚካኤል በፈረስ ስማቸው “አባ ሻንቆ” እየተባሉ ይታወቃሉ፡፡ በወሎ ዩኒቨርስቲ በታሪክ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር እና “ሚካኤል፡ ንጉሠ ወሎ ወ ትግሬ” መጽሐፍ ጸሐፊ ዶክተር ምሰጋናው ታደሰ እንዳስረዱት የደሴ ከተማ መስራች፣ የወሎው ባላባት፣ የልጅ እያሱ አባት፣ የእቴጌ መነን አያት ንጉስ ሚካኤል በዛሬዋ ዕለት ጥር 27/1842 ዓ.ም ነበር የተወለዱት፡፡
ንጉስ ሚካኤል በ1870 ዓ.ም የወሎ ገዥነታቸው በአፄ ዮሐንስ 4ኛ በቦሩ ሜዳ በተደረገ ጉባዔ ላይ ራስ የሚል ማዕረግ ተሰጣቸው፡፡ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመንም ከቤተ መንግሥት ጋር የጋብቻ ትስስር መፍጠራቸው ስማቸው በይበልጥ እንዲታወቅ አስቻላቸው፡፡ ቀስ በቀስ ግዛታቸውን እያጠናከሩ ሄዱ፡፡ በልጃቸው በአቤቶ ኢያሱ ዘመን ደግሞ ሰፊ ግዛት ተጨምሮላቸው በንጉሥነት ማዕረግ ከፍ ብለው የሰሜኑን የሀገሪቱን ክፍል በእርሳቸው አስተዳደር ሥር ሆኖ ነበር፡፡
ንጉሥ ሚካኤል የወሎ፣ የትግሬ፣ የበጌምድርና ጎጃም ንጉሥ ተሰኝተው ከሸዋ የአፄ ምኒልክን ካባና ዘውድ በማስመጣት ደሴ ላይ በመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የንግሥና ሥነ ሥርዓት ፈጽመዋል፡፡ ንጉስ ሚካኤል የግዛታቸውን ዋና መቀመጫ ከተንታ ወደ ደሴ አዘዋውረው የከተሙበት እንዲሁም ቤተመንግሥታቸውን፣ የግብር አዳራሻቸውን፣ አብያተ ክርስትያናትን እና ልዩ ልዩ ተቋማትን አስገነቡ፡፡
የደሴን ከተማ ከወታደራዊ ስትራቴጅነት ባሻገር የባህል፣ የማኅበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ማዕከል በማድረግ አስፋፍተዋል፡፡ ንጉሱ በአስተዳደራቸው በኩል በተለይም በወሎ ሕዝብ ዘንድ ልዩ አክብሮትና ፍቅርን ማሳደር ችለው ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ የወቅቱን ሁኔታ ከነ ድባቡ የሚመሰክረው የግብር አዳራሻቸው “አይጠየፍ” ሁሉንም ያላንዳች ልዩነት በእኩልነት ሲያስተናግዱ የቆዩበት መልካም ልማድ ታሪኩ ብቻ ሳይሆን ሁሉን በእኩል የማየት እሴቱ አሁን ድረስ ዘመንን እንዲሻገር ረድቷል፡፡
ወቅቱ ብልጣብልጦቹ የአውሮፓ ሃያላን ቅኝ ገዥዎች የውስጥ ችግሮችን በማባባስ “በለያይተህ ግዛ መርህ” ለአንድ ወገን ድጋፍ በመስጠት በሌላኛው ወገን ላይ ቅራኔ በማነሳሳት የራሳቸውን የኃይል ሚዛን ለማስጠበቅ እንደ ዓይነተኛ መሣሪያ ተጠቅመውበታል፡፡ ንጉሥ ሚካኤል ግን ሀገራቸው በባዕድ ወራሪ ሲያጋጥማት ምንም እንኳን የውስጥ ቅራኔ ቢኖርም የባዕዳኑን ድለላ ወደ ጎን ትተው በጋራ ትብብር የሀገራቸውን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ረገድ አይተኬ ሚና ነበራቸው፡፡
ዶክተር ምስጋናው እንዳስረዱት ራስ ሚካኤል የዳግማዊ ምኒልክን የክተት ጥሪ ተቀብለው የወሎን ጦር ወደ ታሪካዊው የዓድዋ ዘመቻ አዝምተዋል፤ ጀግንነታቸውንም በጦሩ ሜዳ ውሎ በአካል ተሰልፈው አሳይተዋል፡፡
ንጉስ ሚካኤል በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውን የቅኝ ገዥዎች አደጋ በቆራጥነት የተከላከሉ መሆናቸውን ታሪክ አይዘነጋውም፡፡
አፄ ሚኒልክ የአድዋ ጦርነትን ለማካሄድ “በጥር ጦርነት አለብኝ ወረኢሉ ከተህ ጠብቀኝ” ብለው አዋጅ አስነገሩ፡፡ ጦሩም ቀጠሮውን ጠብቆ ወረኢሉ ሲከት ንጉስ ሚካኤል ጦሩን መንገድ በመምራት፣ የከተተውን ሠራዊት እግር በማጠብና ቀለቡን አዘጋጅተው ሠራዊቱን በማስተናገድ ትልቁን ድርሻ ተወጥተዋል፡፡
ዘማቹ ሠራዊት ወኔ እንዳይሸሸው ሞራል ለመገንባት የተገኙትን የጥበብ ሰዎች፣ ጦሩን በፀሎት ለማገዝ የተሳተፉትን ካህናት አባቶች በማስተናገድ በኩልም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን የነገስታት ዜና መዋዕል አትቶታል፡፡
የጣሊያን በአድዋ ዘመቻው ላይ ከንጉሰ ነገስቱ ከአፄ ሚኒልክ ቀጥሎ በቁጥር በርካታ ቁጥር ያለው ጦር በማሰለፍ ውጊያው በድል እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በአካል በመገኘት በሦስት ግንባር ተዋግተዋል፡፡ ለዚህም በወቅቱ
“ማን በነገረው ለጣሊያን ደርሶ፣
ሚካኤል መጣ ረመጥ ለብሶ፤” ተብሎ የተገጠመላቸው ንጉስ ሚካኤል ናቸው፡፡
ታሪኩ ብዙ ነው፤ ጀብዱ ተወርቶ አያልቅም፤ ዛሬ እኝህን ንጉስ ስንዘክር ኢትዮጵያ “በቅኝ ግዛት ስር ያልወደቀች፣ የራሷ ማንነት ያላት” ሲባል የእነዚህን የጥንት መሪዎች የመስዋዕትነት ታሪክ በውል መረዳት ግድ ይላል፡፡ መረዳት ብቻ ሳይሆን በዛ ልክ ሠርቶ ሀገርን ማሻገር ግድ እንደሚል የታሪክ መምህሩ እና ጸሐፊው ዶክተር ምስጋናው አብራርተዋል፡፡
በትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

Previous articleየህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ሦስት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል፡፡
Next articleበኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ወደ ምርት ያልገቡ ፋብሪካዎችን ሥራ ለማስጀመር 9 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እንደተመደበ ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡