
የሁለተኛው ዙር የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት እና የምግብ ዋስትና ፕሮግራም በ550 ሚሊዮን ዶላር በጀት በ100 ከተሞች ተግባራዊ ይደረጋል ተባለ፡፡
ባሕር ዳር ፡ ጥር 27/2013 ዓ.ም (አብመድ)
ሁለተኛው ዙር የአማራ ክልል የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት እና የምግብ ዋስትና ፕሮጀክት የማብሰሪያ ውይይት በወልድያ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በውይይቱ እንደተነሳው አሳዳጊ አልባ ህፃናት፣ ጧሪ እና ደጋፊ የሌላቸው አረጋውያን እንዲሁም በተደራራቢ አካል ጉዳት ምክንያት መሥራት የማይችሉ አካል ጉዳተኞች በዚህ ፕሮጀክት በቀጥታ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎችም በተለያዩ የፅዳትና ውበት እና የተለያዩ አነስተኛ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ተሳታፊ በመሆን ኑሮዋቸውን እንዲያሻሻሉ ይደረጋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ለጎዳና ተዳዳሪነት የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችም የስነልቦና ተሀድሶ ከተደረገላቸው በኋላ በፕሮጀክቱ የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማም ዜጎች ሠርተው የሚለወጡበትና ከድህነት የሚወጡበት ይሆናል፡፡ ለዚህም በየደረጃው ያሉ የሥራ ኀላፊዎች ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ መልዕክት ተላልፏል፡፡
በመጀመሪያው ዙር የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት እና የምግብ ዋስትና ፕሮግራም በሀገር አቀፍ ደረጃ በ11 ከተሞች በ450 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተግባራዊ የተደረገ መሆኑ ተነስቷል፡፡
በአማራ ክልል የመጀመሪያው ዙር ተሳታፊ የሆነችው የደሴ ከተማ አፈፃፀም ውጤታማ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ በመጀመሪያው ዙር በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሳታፊ የነበሩት 11 ከተሞች በሁለተኛው ዙር በአዲስ ከተካተቱት 72 ከተሞች ጋር አብረው እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡
የሁለተኛው ዙር የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት እና የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ከዓለም ባንክ በተመደበ 400 ሚሊዮን ዶላርና በፌዴራል መንግሥት ከተመደበ 150 ሚሊዮን ዶላር በጠቅላላ በ550 ሚሊዮን ዶላር በጀት በሀገር አቀፍ ደረጃ በ100 ከተሞች ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡
የሁለተኛው ዙር አተገባበር ላይ በወልድያ ከተማ እየተካሄደ ያለው የውይይት መድረክ እሰከ ጥር 29/2013 የሚቀጥል ይሆናል፡፡ የውይይት መድረኩ በፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ፣ በአማራ ክልል ቴክኒክና ሙያ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ የጋራ ትብብር ነው የተዘጋጀው፡፡
ዘጋቢ፡- ተስፋ ሞላ–ከወልደያ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ