በአማራ ክልል ከ40 በላይ የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት ቢኖሩም እሴት ጨምሮ ለገቢያ በማቅረብ የሚገኘው ገቢ ዝቅተኛ መሆኑ ተገለጸ፡፡

865
በአማራ ክልል ከ40 በላይ የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት ቢኖሩም እሴት ጨምሮ ለገቢያ በማቅረብ የሚገኘው ገቢ ዝቅተኛ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 26/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ ከ40 በላይ ባለ ብዙ ቀለም የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ የጌጣጌጥ ማዕድናት ውስጥ ኦፓልን ጨምሮ የተለያዩ ማዕድናት በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ልዩ ስሙ ወገል ጤና በተባለው አካባቢ በብዛት ይገኛሉ፡፡
የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት በክልሉ በብዛት ይገኙ እንጅ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለአካባቢው ማኅበረሰብም ሆነ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ዝቅተኛ ነው፡፡ ማዕድናትን በጥሬው (እሴት ሳይጨመርባቸው) ለገበያ ከማቅረብ ይልቅ እሴት ጨምሮ ማቅረብ ተገቢ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ከሦስት ዓመታት ጀምሮ ሚዳ እምርታ ፕሮጀክት ወደ ወረዳዎች ገብቶ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡ ወጣት ትዕግስት ካሰው የከበሩ ማዕድናትን በመቁረጥና በማስዋብ ሥራ ላይ ተሰማርታለች፡፡ እንደ ትዕግስት ገለጻ አማራ ክልል የበርካታ የከበሩ ማዕድናት ባለቤት ቢሆንም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ባለመኖራቸው ከዘርፉ መጠቀም አለመቻሉን ነግራናለች፡፡
ትዕግስትና ጓደኞቿ የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናትን ለገበያ ሲያቀርቡ ከመቁረጥ ውጭ ምንም አይጨምሩም ነበር፤ በፕሮጀክቱ ስልጠናና የማሽን ድጋፍ በማግኘታቸው የተለያዩ ጌጣጌጦችን ማምረት ጀምረዋል፡፡ በዚህም ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ትዕግስት ማዕድናቱ እሴት ተጨምሮባቸው ሲወጡ ለሀገርም ሆነ ለማኅበረሰቡ ጥቅም ይሰጣሉ ብላለች፡፡ ማኅበረሰቡም የሀገሩን የከበሩ ጌጣጌጦች በመጠቀም ለሌሎች ቢያስተዋውቅ፤ መንግሥትም ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ ማዕድናቱ እሴት ተጨምሮባቸው የሚወጡበትን መንገድ ቢያመቻች የሚል ሃሳብ አላት፡፡
አቶ አደራው ዳኛው በሚዳ እምርታ ፕሮጀክት የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት ልማት አስተባባሪ ናቸው፡፡ የዓለም ባንክ ያደረገውን ጥናት ጠቅሰው በአማራ ክልል ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ከ40 በላይ የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናትን እሴት ጨምሮ ለገቢያ በማቅረብ የሚገኘው ገቢ ዝቅተኛ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡ እንደ አቶ አደራው ገለጻ በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ የሚገኘው የኦፓል ምርት በዓለም ገበያ ተመራጭነት አግኝቷል፡፡
ሚዳ እምርታ ፕሮጀክት ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም ድህነትን ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን ነው አስተባባሪው የገለጹት፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናትን ቆርጠው ከመሸጥ ወጥተው ጌጣጌጦችን አምርተው ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረቡ እንደሆነም ነግረውናል፡፡ እንደ አቶ አደራው መረጃ ሚዳ በዓለም ከስልሳ ሀገራት ጋር በቅንጅት ይሰራል፡፡ ነገር ግን በከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት ላይ የሚሰራ በኢትዮጵያ ብሎም በአማራ ክልል ብቻ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ አምራቾች እሴት በመጨመር ምርቱን ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡበትን መንገድ እያመቻቸ ነው፡፡ “በየዓመቱ ከሀገሪቱ የሚወጣው የከበረ የጌጣጌጥ ማዕድን በጥሬው እየወጣ በመሆኑ የስራ እድሉንም ሆነ ገቢውን አሳልፈን ለሌላ ሀገር እየሰጠን ነው” ብለዋል፡፡ እንደ አስተባባሪው ገለጻ ክልሉ በምግብ ዋስትና ያስመጣቸው 17 ያህል ማሽነሪዎች አሉ፤ አጠቃቀማቸውን በተመለከተ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
አቶ በትሩ ኀይሌ በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የማዕድን ግብይት ሥራዎች ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደ አቶ በትሩ ገለጻ ሚዳ እምርታ ፕሮጀክት መንግሥት መሸፈን ያልቻለውን በመሸፈን ለበርካታ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡ ማዕድን በሀገርና በመንግሥት አቅም ብቻ ፈልጎ ማግኘት ከባድ በመሆኑ እንደሚዳ ያሉ ፕሮጀክቶችን በማፈላለግ ከአጋር አካላት ጋር መሥራት እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
ዓለምአቀፍ ድርጅቶች እውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን እና የሥራ ባህላቸውን ይዘው እንዲመጡ እና እኛ ካለን የሰው ኀይልና የተፈጥሮ ሀብት ጋር ለማስተሳሰር እየተሰራ እንደሆነ ነው ዳይሬክተሩ የነገሩን፡፡ የሀገራችንን የከበሩ የጌጣጌጥ ማእድናት እና ሌሎችን የተፈጥሮ ሀብቶች ለዓለም ማስተዋወቅ ተገቢ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ2010 እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ እሴት ሳይጨመርባቸው ከተላኩ የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት ሽያጭ ማግኘት ያለባትን ከ226 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር ገቢ እንዳጣች ከፕሮጀክቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ዘጋቢ፡-ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

Previous articleበባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በጣና ክፍለ ከተማ በሕገ ወጥ መንገድ በግለሰብ ቤት የተከማቸ 11 በርሚል ነዳጅ እና ቤንዚን በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡
Next articleበአዲስ አበባ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 15 የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ።