
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በጣና ክፍለ ከተማ በሕገ ወጥ መንገድ በግለሰብ ቤት የተከማቸ 11 በርሚል ነዳጅ እና ቤንዚን በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 26/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች የነዳጅ በተለይም የቤንዚን እጥረት ጎልቶ ይስተዋላል፡፡ የንግድ ሚኒስቴር የነዳጅ እጥረት የለም ቢልም የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በሀገሪቱ ነዳጅን በፍትሓዊነት በመጠቀም ዙሪያ ችግር አለ ሲል ይሰማል፡፡
የነዳጅ እና ቤንዚል ጥቁር ገበያ ለእጥረቱ አንድ ምክንያት ተደርጎም ይወሰዳል፡፡
ጥር 25/2013 ዓ.ም ከሕዝብ በደረሰ ጥቆማ መሰረት የባሕር ዳር ከተማ ንግድ መምሪያ፣ የጣና ክፍለ ከተማ ንግድ ጽሕፈት ቤት፣ የከተማዋ የፀጥታ ኃይል እና ፖሊስ በጋራ ባደረጉት ዘመቻ በሕገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ነዳጅ እና ቤንዚን ተይዟል፡፡ በጣና ክፍለ ከተማ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ 11 በርሜል ነዳጅ እና ቤንዚን እንዲሁም ለጥቁር ገበያ የተዘጋጀ ቤንዚን በ20 ባለሁለት ሊትር የውኃ ማሸጊያ ሃይላንድ በቁጥጥር ስር ማዋሉን በባሕር ዳር ከተማ ፖሊስ መምሪያ የ6ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ንብረት ተፈራ ገልጸዋል፡፡
ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እየተካሄደ ነው ተብሏል፡፡ የተያዘው ነዳጅ እና ቤንዚን የዘርፉ ፈቃድ በሌለው ግሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው ያሉት ምክትል ኢንስፔክተር ንብረቱ ለጥቁር ገበያው መበራከት ምክንያት የሆነውን እጥረት መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡
ሕዝቡ ተመሳሳይ ጥቆማዎችን በመስጠት ከፖሊስ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከሚስተዋለው የነዳጅ እና ቤንዚን እጥረት በተጨማሪ ያለውን በፍትሓዊነት ለተጠቃሚ በማድረስ በኩል እጥረት መኖሩንም የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሠላም እና የሕዝብ ደኅንነት መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል አብየ አምበል ተናግረዋል፡፡
ከማደያዎች ጋር በመመሳጠር ቤንዚል እና ነዳጅ በሕገ ወጥ መንገድ ወጥቶ በጥቁር ገበያ እንደሚሸጥ መረጃዎች እየደረሳቸው መሆኑን ኮሎኔል አብየ በተለይም ለአብመድ ገልጠዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ የሚስተዋለውን የነዳጅ የጥቁር ገበያ እንቅስቃሴ ለመቀነስ ንግድ፣ ፀጥታ፣ ደንብ ማስከበር እና ሕዝቡ በጋራ እየሰሩ ነው ተብሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህ ዜና በሚጠናቀርበት ወቅትም በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ በርካታ ማደያዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎች ተሰልፈው ሲጠብቁ አስተውለናል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ