
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ስምንት የመንገድ ፕሮጀክቶችን የኮንትራት ስምምነት ተፈራረመ።
ባሕር ዳር፡ ጥር 26/2013 ዓ.ም (አብመድ) በተያዘው 2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የ13 የመንገድ ፕሮጀክቶች የኮንትራት ስምምነት መፈራረሙን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል። በበጀት ዓመቱ በ43 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በጀት ወጪ 21 የመንገድ ፕሮጀክቶች ሥራ ይጀመራል ተብሏል።
እንደ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መረጃ የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ሥራ 1 ሺህ 774 ኪሎ ሜትር ርዝመት ይሸፍናል። ዛሬ የተፈረሙት የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል በአማራ ክልል ለረጅም ዓመታት ደረጃቸው እንዲሻሻል በሕዝብ ጥያቄ ሲቀርብባቸው ነበሩ አካባቢዎችን አካቷል፡፡
ደብረ ማርቆስ – ደብረ ኤልያስ – ተምጫ – ቁጭ – አየሁ – ዚገም – ቻግኒ ኮንትራት ሦስት ቁጭ – አምበላ መንገድ ፕሮጀት ጠቅላላ 78 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር አንዱ ነው፡፡
ዱርቤቴ-ቁንዝላ-ገላጎ-መተማ፣ ሎት ሦስት ገላጎ-ገንዳ ውኃ መንገድ ዲዛይንና ግንባታ ሥራም 125 ኪሎ ሜትር ይገኝበታል፡፡
73 ኪሎ ሜትር ዳንግላ – ጃዊ ዲዛይንና ግንባታ መንገድ ሥራ ፕሮጀክትም በስምምነቱ ተካቷል፡፡ 35 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር ማንኩሳ – ብርሸለቆ -142 ቀበሌ ዲዛይንና ግንባታ መንገድ ሥራ ፕሮጀክት በስምምነቱ ከተካተቱት ውስጥ ይገኝበታል፡፡
በተደረገው ስምምነት እንደስላሴ – ራማ ገረሁ ሰናይ ፕሮጀክት ከኤርትራ፣ ዱርቤቴ – ቁንዝላ – ገላጎ – መተማ ከሱዳን፣ ነጌሌ ቦረና – ዶሎ አዶ – መልካ ኩፍቱ ከኬንያና ሶማሊያ የሚያገናኙ ናቸው ተብሏል።
በዓመቱ ከሚገነቡ 21 ፕሮጀክቶች ውስጥ 20ቹ በኢትዮጵያ መንግሥት ወጪ የሚገነቡ መሆናቸውም ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- ዘመኑ ታደለ – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ