
በትራንስፖርት ስምሪት ችግር ሥራቸውን በሚፈልጉት ጊዜና ፍጥነት ለማከናወን መቸገራቸውን ተሳፋሪዎች ተናገሩ፡፡
ችግሩ ወቅታዊ መሆኑን እና በአጭር ጊዜ መፍትሔ እንደሚያገኝ የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ አስታውቋል፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 26/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አንከሻ ጓጉሳ ወረዳ ግምጃ ቤት ከተማ በሚገኘው መናኽሪያ የሕዝብ ትራንስፖርት ስምሪት ችግር ነዋሪዎች በሚፈልጉት ጊዜ እና ፍጥነት ደርሰው ሥራቸውን ለማከናወን መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡
የአንካሻ ጓጉሳ ወረዳ ግምጃ ቤት ከተማ በቅርቡ የከተማ አስተዳደርነት ጥያቄ መልስ ካገኙ የክልሉ ከተሞች አንዷ ናት፡፡ ከተማዋ ወደ ከተማ አስተዳደርነት ማደግ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ያገኛሉ ብለው ተስፋ የሰነቁ ነዋሪዎች በአደባባይ ደስታቸውን ሲገልፁ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
ሁሉም የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአንድ ጀንበር ይፈታሉ ተብሎ ባይታሰብም በቀላሉ መፍትሔ ማግኘት ያለባቸው ጉዳዮች ግን መፍትሔ ማግኘት እንዳለባቸው ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ኃይለማሪያም ቢተው ለሥራ ጉዳይ ከግምጃቤት ወደ እንጅባራ ከተማ ለመንቀሳቀስ በተፈጠረው የትራንስፖርት እጥረት ምክንያት መጉላላታቸውን ነግረውናል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በግምጃቤት ከተማ በሚገኘው መናኽሪያ በቂ የሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ እየተመደበ አይደልም፤ ይህም ከፍተኛ መጉላላት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
ወይዘሮ ሐመልማል ወልዱም በየቀኑ ከግምጃቤት ወደ እንጅባራ ከተማ በመመላለስ የዕለት ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት መናኽሪያ በተፈጠረው የተሸከርካሪ ስምሪት ችግር ደግሞ የሚፈልጉትን ሥራ በፈለጉት ሠዓትና ደርሰው ማከናወን አለመቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት ያለአግባብ እንዲባክን እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ስለ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ከባለሃብቶችና አሽከርካሪዎች ጋር በመነጋገር ፈጣን ምላሽ መስጠት አለባቸውም ነው ያሉት፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር መንገድ እና ትራንስፖርት መምሪያ ኀላፊ መኮንን ላዋየው እንደገለጹት በብሔረሰብ አስተዳደሩ በ176 መስመሮች በየሳምንቱ ከ750 እስከ 800 ተሸከርካሪዎች ተመድበው ለሁሉም ወረዳዎች አግልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረው መጉላላትም ከስምሪት ችግርና ከተሸከርካሪ እጥረት ሳይሆን ከወቅታዊ በዓላትና ሰርግ ጋር ተያይዞ ነው ብለዋል፡፡ ይህም ቢሆን ወቅቱን ምክንያት በማድረግና ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማገኘት ከተሰጠው ስምሪት ውጭ የሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎችን ለመከታተል ከመምሪያው የባለሙያዎችና አስተዳደር አባላት ስምሪት ወስደው ወደ ሁሉም ወረዳዎች መንቀሳቀሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ችግሩም በአጭር ጊዜ መፍትሔ እንደሚያገኝ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በፊት ያልተገባ ጥቅም ለማገኘት ኅብረተሰቡን ያጉላሉና ከታሪፍ በላይ ገንዘብ የጠየቁ አሽከርካሪዎች ላይ ተገቢ የእርምት እርምጃ መወሰዱንም ጠቅሰዋል፡፡ አሽከርካሪዎች ‹‹ከአዩኝ አላዩኝ›› አሰራር በመውጣት ኅብረተሰቡን በቅንነት ማገልገል እና ራሳቸውንም ተገቢ ካልሆነ ቅጣት መታደግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ