የግብርናው ዘርፍ የነበሩበትን ችግሮች በመቋቋም ሊደርስ የሚችለውን ሀገራዊ የምጣኔ ሀብት ውድቀት መታደግ መቻሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

326
የግብርናው ዘርፍ የነበሩበትን ችግሮች በመቋቋም ሊደርስ የሚችለውን ሀገራዊ የምጣኔ ሀብት ውድቀት መታደግ መቻሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 25/2013 ዓ.ም (አብመድ) የግብርና ሚኒስቴር ከክልል ግብርና ቢሮዎች፣ከተጠሪ ተቋማት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የ2013 ዓ.ም የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ አካሂዷል፡፡ ግብርናው ዘርፍ ከመቸውም ጊዜ በላይ በተያዘው በጀት ዓመት የተለያዩ ችግሮች ገጥሞት እንደነበር ተነስቷል፡፡ በዚህም የዓለምን ኢኮኖሚ እንዲያሽቆለቁል ያደረገው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ ለግብርና ሥራ ዋና ማነቆ እንደሆነ እና በሀገራችን ብሎም በጎረቤት ሀገሮች የተከሰተው የበርሃ አንበጣ ወረርሽኝ ሌላ ፈተና እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
ባለፈው የክረምት ወቅት ከፍተኛ ጎርፍ መከሰቱ በሰፋፊ መሬቶች ላይ ጉዳት ማድረሱ በመጨረሻም በሀገራችን በተከሰተው የሀገር ክህደት ተግባር ህግን የማስከበር ሥራ ጋር ተያይዞ የግብርና ሥራዎችን ለማከናወን እና የመረጃ ፍሰት ላይ ከፍተኛ ማነቆዎች እንደነበሩ በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡
ሆኖም ግን የግብርና ሚኒስቴር ከክልሎች፣ ከተጠሪ ተቋማት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ወቅቱ የሚጠይቀውን አመራር በመስጠት በሀገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ውድቀት እንዳይደርስ ፈርጀ ብዙ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል ተብሏል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ሊደርስባት ከሚችለው የምጣኔ ሀብት ውድቀት መታደግ መቻሉን ነው የተገለጸው፡፡
ለአብነት ባለፉት ስድስት ወራቶች ብቻ 240 ሚሊዮን ዶላር የገቢ ምንጭ ያስገኘውን እና የወደፊቱ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት የለውጥ ሞተር መሆን በሚችለው በሆርቲካለችር ዘርፉ የተፈጠሩትን ችግሮች ተቋቁሞ ጥሩ ውጤት አስመዝግቧል ተብሏል፡፡ የግብርና ምርትና ምርታማነት በብዛትና በጥራት እንዲጨምር ለማድረግ የግብዓት አቅርቦት ዋናውን ሚና ይወስዳል፡፡ በዚህም የአፈር ማዳበሪያ ከመቸውም ጊዜ በላይ ቀድሞ እየገባ መሆኑ ተነስቷል፡፡
ግብርና ሚኒስቴር የግብዓት ግብይት ዘርፍ፣ ከክልሎች እና ከጅቡቲ ወደብ እስከ አርሶአደሩ እሰኪደርስ ባለው ሂደት ውስጥ ከሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመናበብ ግብዓቱ ወቅቱን ጠብቆ እንዲደረስ ከፍተኛ ሥራ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡ የግብዓት አቅርቦት በወቅቱ ለአርሶ አደሩ መድረሱ በተለይ በእርሻ ልማት ዘርፍ ላይ እየተከናወነ ለሚገኘው ምርት እና ምርታማትን በብዛትና በጥራት አምርቶ የሀገራችንን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ በሚደረገው ርብርብ ከፈተኛ ሚና ይኖረዋል ብሏል ሚኒስትሩ፡፡
የተፈጥሮ ሀብት እና ምግብ ዋስትና ልማት ዘርፍን አስመልክቶ በአሁኑ ወቅት በሁሉም ክልሎች የተፋሰስ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆነቸው ተጠቅሷል፡፡ ከመስኖ ግንባታ እና ልማት፣ ከሥራ እድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ ሰፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑ በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡
በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ከዝርያ ማሻሻል፣ የእንስሳት ጤና እና የዘርፉ ሥራዎች ላይ አበረታች ዉጤቶች ተመዝግቧል ተብሏል፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን የቀጣይ የግብርናን እድገት ሊወስኑ ከሚችሉ የትኩረት መስኮች የሆርቲካቸር ዘርፉ እና የመስኖ ቆላ ስንዴ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ ምንጭ፡-ግብርና ሚኒስቴር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ቀደምት አያቶቻችን እንኳን ለመንግሥት ለአእዋፋትና ለዱር እንስሳት አውድማ ላይ ትተው ይሄዱ ነበር” ተሾመ አየለ (ባለሀገሩ) የታማኝ ግብር ከፋይ አምባሳደር ተሸላሚ
Next articleበትራንስፖርት ስምሪት ችግር ሥራቸውን በሚፈልጉት ጊዜና ፍጥነት ለማከናወን መቸገራቸውን ተሳፋሪዎች ተናገሩ፡፡