“ቀደምት አያቶቻችን እንኳን ለመንግሥት ለአእዋፋትና ለዱር እንስሳት አውድማ ላይ ትተው ይሄዱ ነበር” ተሾመ አየለ (ባለሀገሩ) የታማኝ ግብር ከፋይ አምባሳደር ተሸላሚ

825
“ቀደምት አያቶቻችን እንኳን ለመንግሥት ለአእዋፋትና ለዱር እንስሳት አውድማ ላይ ትተው ይሄዱ ነበር” ተሾመ አየለ (ባለሀገሩ) የታማኝ ግብር ከፋይ አምባሳደር ተሸላሚ
ባሕር ዳር፡ ጥር 25/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ለታማኝ ግብር ከፋዮችና ታታሪ ሠራተኞች ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ሙሀመድ አብዱ አሊ በደሴ ከተማ በንግድ ሥራ ነው የሚተዳደሩት ከንግድ ሥራቸው ከሚያገኑት ግብር 44 ሚሊዮን 287 ሺህ 815 ብር ዓመታዊ ግብር ለመንግስት ከፍለዋል እያንዳንዱን ግብይታቸውን የሚፈፅሙት ደረሰኝ በመቁረጥ ነው፡፡
ለዚህ ሀገራዊ ኀላፊነት የመወጣት ተግባራቸውም የአማራ ክልል ገቢወች ቢሮ የታማኝ ግብር ከፋይ እውቅና ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡ ተሸላሚው ግብር ከፋይ ሙሀመድ አብዱ እደሚሉት ግብር የሚከፍሉት ደስ እያላቸው ነው፡፡
ሌላው ግብር በመክፈል ተሸላሚና የግብር አምባሳደር የባለ ሀገሩ አስጎብኝ ድርጅት ባለቤት አቶ ተሾመ አየለ (ባለሀገሩ) ናቸው፡፡ የአምባሳደርነት እውቅና ሲሰጣቸው ባስተላለፉት መልዕክት “ቀደምት አያቶቻችን እንኳን ለመንግሥት ለአእዋፋትና ለዱር እንስሳት የሚገባውን አውድማ ላይ ትተው ይሄዱ ነበር” በማለት ቀደም ብሎ በባህል ግብርን በታማኝነት የመክፈል ልምድ መኖሩን አስታውሰዋል፡፡
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የተሻለ ገቢ እንዲሰበስብ በትጋት ሲሠሩ ለነበሩ ባለሙያዎች፣ ለታማኝ ግብር ከፋዮች፣ ገቢ በመሰብሰብ በስድስት ወራቱ የተሻለ አፈጻጸም ለነበራቸው ወረዳዎች፣ ዞኖች፣ ከተሞችና ክፍለ ከተሞች እውቅናና ሽልማት ሰጥቷል፡፡ የተሻለ አበርክቶ የነበራቸው ነባር የግብር አምባሳደሮችም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፤ አምባሳደርነታቸው ታድሶላቸዋል፡፡
በግንዛቤ ፈጠራ የተሸለ አፈጻጸም የነበራቸው አዳዲስ አምባሳደሮችም ተሸልመዋል፡፡ የቢሮው ኀላፊ ወይዘሮ ብዙአየሁ ቢያዝን እንዳሉት በያዝነው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ግብር ስብሰባ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አለው፡፡
የኮሮና ተጽዕኖን፣ ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር እንዲሁም ሌሎች ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በመጋፈጥ የተገኘ ውጤት በመሆኑም አበረታች ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም የተቋሙ የመፈጸም አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑ፣ አዳዲስ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱ፣ ግብር የመክፈል ባሕል እያደገ መምጣትና የባለድርሻ አካላት ሚና ጉልህ እንደነበር አንስተዋል፡፡
ሆኖም በየደረጃው ያሉ መሪዎች የቁርጠኝነትና ተቀናጅቶ የመሥራት ልምድ ወጥ አለመሆን፣ የታክስ ሕግ በተመሳሳይ መልኩ አለመተግበሩና የታክስ ማጭበርበር ችግሮች በግማሽ ዓመቱ ለመሥራት የታቀደውን ማሳካት አለመቻሉን አንስተዋል፡፡ ችግሮቹ እንዲፈቱ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሠራም ነው የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የመከላከያ ሰራዊት ጁንታውን ብቻ ሳይሆን የጁንታውን ርዝራዦችና የፖለቲካ ደላሎችን ጭምር ደምስሷል” ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ
Next articleየግብርናው ዘርፍ የነበሩበትን ችግሮች በመቋቋም ሊደርስ የሚችለውን ሀገራዊ የምጣኔ ሀብት ውድቀት መታደግ መቻሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡