
አገልግሎት ሳይሰጥ የፈረሰው የአንኮበር ዱለሳ አስፓልት መንገድ በማህበረሰቡ ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡
“ግንባታውን ያከናወንኩት በተቀመጠው ዲዛይን መሠረት ነው” ሰንሻይን ኮንስትራክሽን፡፡
“መንገዱን ለማስተካከል ጥናት እያሠራሁ ነው” የኢትዪጵያ መንገዶች ባለስልጣን፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 25/2013 ዓ.ም (አብመድ) ከአንኮበር ቤተ መንግሥት እስከ ዱለሳ የተሠራው የአስፓልት መንገድ የደብረብርሃን – አዋሽ አርባ የአስፓልት መንገድ አንዱ አካል ነው፡፡ የዚህ የመንገድ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ከጅቡቲ ወደብ ጋር አስተሳስሮ ወጪና ገቢ ንግድን በማሳለጥ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እዲኖረው የታሰበ ነው፡፡ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለሚታይባት ደብረብርሃን ከተማና አካባቢዋም ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ዕድል ይፈጥራል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ታደሰ ገብረጻድቅ እንዳሉት የአካባቢው ሕዝብ መንገዱ እንዲሠራ ለዘመናት ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡ ግንባታው በ2009 ዓ.ም የተጀመረው የመንገድ ፕሮጀክቱ በ2012 ዓ.ም ቢጠናቀቅም ለምረቃ አልበቃም፣ የታለመለትን አገልግሎት መስጠትም ተስኖታል ብለዋል፡፡ በተለይ ከአንኮበር ቤተ መንግሥት እስከ አልዩ አምባ የሚዘልቀው 12 ኪሎሜትር መንገድ የመንሸራተትና የመስመጥ አደጋ አጋጥሞታል፡፡
ይሕም በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ መፍጠሩን ነው ዋና አስተዳዳሪው የተናገሩት፡፡ “የሕዝቡ ፍላጎት መንገድ ተሠርቶ እንዲፈርስ ሳይሆን እንዲጠቀምበት ነው፤ ከፍተኛ ሀብት ወጥቶበት ጥቅም ሳይሰጥ የሚፈርስ ከሆነ ተሠራም አልተሠራም ለውጥ የለውም” በማለትም ተናግረዋል፡፡ አቶ ታደሰ እንዳሉት ሕዝቡ በፍጥነት እንዲስተካከል ጠይቋል፡፡
አብመድ ስለጉዳዩ የጠየቀው የመንገድ ፕሮጀክቱ ተቋራጭ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ግንባታውን ያከናወነው በተቀመጠው ዲዛይን መሠረት መሆኑን አስታውቋል፡፡ በሰንሻይን ኮንስትራክሽን የምሕንድስና መምሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አቤሴሎም ደመቀ እንደተናገሩት የአስፓልት መንገዱ የተገነባው ያለምንም የጥራት ችግር ነው፡፡ ለዚህም እያንዳንዱ የግንባታ ሥራ በአማካሪ መሀንዲስ የተረጋገጠ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ቀደም ብሎ የተሠራው የዲዛይን ጥናት የመሬቱን ተፈጥሯዊ ባህሪ ያላገናዘበ በመሆኑ ችግሩ መፈጠሩን አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የመሬት መንሸራተት ችግሩ የጀመረው የአፈር ቆረጣና የውኃ ማፋሰሻ ሥራው ከተገባደደ በኋላ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በባለስልጣኑ የማዕከላዊ ሪጅን ቡድን መሪ ኢንጂነር ተስፋዬ አንተንይስሙህ በሰጡት ማብራሪያ ችግሩ የተፈጠረው ከአቅም በላይ በሆነ ተፈጥሯዊ ምክንት ነው፡፡ አካባቢው ከፍተኛ ዝናብ ያለበት እና ተራራማና ገደላማ አቀማመጥ ያለው በመሆኑ ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ ሆኗል፡፡ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ በአማካሪ ድርጅቱ እና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ጥናት በማሥራት መፍትሔ ለመስጠት ሙከራ መደረጉንም አስረድተዋል፡፡
በተደጋጋሚ የተሠሩ ጥናቶች የሚፈለገውን ውጤት ባለማስገኘታቸውም መንገዱ ባለበት እንዲቆም መደረጉን ነው የተናገሩት፡፡ ችግሩን ለመፍታት በዚህ ወቅት በዘርፉ የተሻለ ልምድና ዕውቀት ባላቸው ሰዎች ጥናት እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ያጋጠመው ችግርና መከናወን ያለባቸው ተግባራት በጥናቱ መለየታቸውን ያስታወቁት ኢንጅነር ተስፋዬ ቀጣይ ለሥራው የሚያስፈልግ ተጨማሪ ገንዘብና ግብአቶች እየተጠኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የጥናቱን ውጤት ተከትሎ ፈጣን የማስተካከያ እርምጃ እደሚወስድም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ