መንግሥት የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ በሠላም አንዲፈታ ያለውን አቋም ማስቀጠሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

266
መንግሥት የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ በሠላም አንዲፈታ ያለውን አቋም ማስቀጠሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ባሕር ዳር ፡ ጥር 25/2013 ዓ.ም (አብመድ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ አንዳስታወቁት በትግራይ ክልል እየተካሄደ የሚገኘው ሰብአዊ እርዳታ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በአሁኑ ጊዜም 92 በሚሆኑ ማእከላት ድጋፍ እየተሰጠ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፓ ግራንቴ እየተደረገ ያለውን ሠብአዊ ድጋፍ በትግራይ ክልል ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ከጉብኝታቸው በኋላ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በጉዳዩ ዙሪያ እና በህግ ማስከበሩ ውጤታማነት ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በሌላ መረጃ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርነትን መረከብ ተከትሎ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጉብኝት በማድረግ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ ኮንጎን ለማረጋጋት ያደረገችውን ወታደራዊ ድጋፍ በማንሳት ለኢትዮጵያ ያላቸውን ክብር ገልጸዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ደቡብ አፍሪካ በኅብረቱ ሊቀመንበርነት ወቅት የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በታማኝነት ስታደራድር መቆየቷን አንስተው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎም ይህን አንደምታደርግ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተመሳሳይ ጉብኝታቸውን በቱኒዚያ ማድረጋቸውም በዚሁ ሳምንት የተከናወነ የዲፖሎማሲ ሥራ መሆኑን አምባሳደር ዲና አንስተዋል፡፡
250 ከሚሆኑ የደቡብ ኮሪያ ባለሃብቶች እና ከአልጀሪያ በፋርማሲ ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ጋር በኢንተርኔት ውይይት እና ገለጻ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
በሳምንቱ በኢትዮ-ሱዳን ዙሪያ በዘርፉ ጥናት ካደረጉ ምሁራን እና የሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ አውደ ርእይ መደረጉን አምሳደር ዲና ተናግረዋል፡፡ የሁለቱን ሀገራት ሰፊ ግንኙነት እና ለአፍሪካም ሆነ ለሁለቱ ሀገራት ጦርነት አዋጭ አለመሆኑን የተሰመረበት ነው ብለዋል፡፡
ሱዳን ያደረገቸውን ወረራ ለማስቆም አሁንም ሠላማዊ መንገድ የተሻለ እና ሁለቱን ሀገራት አሸናፊ የሚያደርግ መንገድ በመሆኑ መንግሥት ይህንኑ አቋሙን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል አምባሳደር ዲና፡፡
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ራይነር በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኩል የኢትዮጵያን ለውጥ ፈጥኖ በመረዳት ሲያደርጉት ለነበረው ድጋፍ ምስጋና ቀርቦላቸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤው የተለያዩ የውሳኔ ሃሳቦችን አጸደቀ፡፡
Next articleአገልግሎት ሳይሰጥ የፈረሰው የአንኮበር ዱለሳ አስፓልት መንገድ በማህበረሰቡ ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡