“እንዲህ ብዙ ሆናችሁ እንደአንድ ስትታዩ ታምራላችሁ” ዶክተር ሂሩት ካሳው

230
“እንዲህ ብዙ ሆናችሁ እንደአንድ ስትታዩ ታምራላችሁ” ዶክተር ሂሩት ካሳው
ባሕር ዳር፡ ጥር 25/2013 ዓ.ም (አብመድ) ዓመታዊ የቅዱስ መርቆሪዎስ ክብረ በዓል በጥንታዊቷ የደብረ ታቦር ከተማ እየተከበረ ነው፡፡ ከባህላዊው የፈረስ ትርዒት ጋር የጠበቀ ቁርኝት እንዳለው የሚነገርለት በአጅባር የሚከበረው ዓመታዊው የቅዱስ መርቆሪዎስ ክብረ በዓል ከሃይማኖታዊ ትርጓሜው ባላነሰ መልኩ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ፋይዳውም የጎላ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዘንድሮው የደብረ ታቦር ቅዱስ መርቆሪዎስ ክብረ በዓል የተገኙት የእለቱ የክብር እንግዳ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ክብረ በዓሉ መንፈሳዊ እና ታሪካዊ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል፡፡
“ዛሬ ከነሙሉ ክብሯ እና ነፃነቷ ለተቀበልናት ሀገር ከአባቶቻችን አጥንት እና ደም በተጨማሪ የፈረሶቻቸው ተጋድሎ ቀላል አልነበረም” ያሉት ሚኒስትሯ ‹‹ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም›› የሚለው ብሂል ለዚህ አውድ የሚሰራ እንዳልሆነም አንስተዋል፡፡
በጥንታዊቷ የበጌ ምድር መናገሻ ደብረ ታቦር ከራስ ጉግሳ ወሌ እስከ ራስ ወንድወሰን ከግቢ እስከ አራዳ የቅዱስ መርቆሪዎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በፈረስ እና ጠጅ ተከብሮ ይውል እንደነበር አውስተዋል ዶክተር ሂሩት፡፡ ይህን በሚገባው መልኩ መዘከር የተግባርም የህሊናም አደራ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ አያይዘውም ዛሬ ፈረስን ለጦርነት የምንጠቀምበት አውድ ባይኖርም ታሪኩን ማሻገር ግን ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ “የቀደመ ታሪኩን በሚገባ የማያውቅ ትውልድ ዛሬን በትርጉም መኖር አይችልም” ብለዋል፡፡ ዶክተር ሂሩት የትምህርት ተቋማት፣ የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሐገር ሽማግሌዎች ትውልዱን በማንቃት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ ሚኒስትሯ ወጣቶች ከቀደመ አባቶቻቸው አኩሪ ታሪክ እና ተጋድሎ ለመማር ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው ነው ያሉት፡፡
ራስን ለሥራ ማዘጋጀት፣ ፍቅርና መደጋገፍን እሴት ማድረግ እና መተጋገዝ እና መረዳዳትን ባህል ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ የበዓሉን ድባብ “እንዲህ ብዙ ሆናችሁ እንደአንድ ስትታዩ ታምራላችሁ” በማለት የገለፁት ሚኒስትሯ የሃያልነት ሚስጥሩ ከመነቃቀፍ ይልቅ መደጋገፍ፣ ከመራራቅ ይልቅ መቀራረብ እና ከመለያየት ይልቅ በጋራ መቆም በመሆኑ እጅ ለእጅ መያያዝ ይገባል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ የፈረስ ትርዒትን ተወዳጅ ስፖርት ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመው የክልል ቢሮዎች፣ የዞን እና የወረዳ አስተዳደሮች ሕዝብን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታው ተጠናቅቆ ጥር 30/2013 ዓ.ም ሊመረቅ ነው፡፡
Next articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤው የተለያዩ የውሳኔ ሃሳቦችን አጸደቀ፡፡