የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታው ተጠናቅቆ ጥር 30/2013 ዓ.ም ሊመረቅ ነው፡፡

375
የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታው ተጠናቅቆ ጥር 30/2013 ዓ.ም ሊመረቅ ነው፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኩ ለሺዎች የሥራ እድል ከመፍጠር ባሻገር የአካባቢዉን ግብርና በማዘመን ታላቅ ሀገራዊ ጥቅም የሚያስገኝ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 25/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጥር 30/2013 ዓ.ም የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምረቃን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሥራ ሲጀምር የውጪ ምንዛሬን እንደሚያሳድግ፣ ግብርናዉን እና ኢንዱስትሪውን በማዘመን ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል እንዲፈጥር ታልሞ የተገነባ መሆኑን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደሴ አሰሜ በሰጡት መግለጫ አስረድተዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ የተጀመረው በ2010 ዓ.ም ነው፡፡ በአጠቃላይ ፓርኩ በ1ሺህ ሄክታር ላይ የሚለማ ሲሆን አሁን ያለው በ260 ሄክተር ላይ መልማቱን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡
ፓርኩ በውስጡ የገበያ ማዕከል፣ የአስተዳደር ሕንፃ፣ ትምህርት ቤት፣ ክሊኒክ፣ የሕፃናት ማቆያ፣ መኖሪያ ቤቶችና ሌሎችም የተሟሉለት ነው፡፡ በፓርኩ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች የተሟሉ መሆኑን ያስረዱት አቶ ደሴ ባለ ሀብቶች ገብተው ሊያመርቱባቸው የሚችሉ ሞዴል ሼዶች የተገነቡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አራት ሼዶች ለሞዴልነት የተገነቡ መሆኑን የገለጹት አቶ ደሴ ባለ ሀብቶች በተገነቡ ሼዶች እንዲገቡ ሳይሆን በራሳቸው የሥራ ባሕሪ መሠረት ሼዶችን በመገንባት እንዲያለሙ ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡
ፓርኩ በውስጡ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ያሟላ በመሆኑ ባለ ሀብቶች ሳይንገላቱ ሥራቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ያስችላቸዋልም ብለዋል፡፡
አቶ ደሴ በሰጡት መግለጫ ከግንባታዉ ጎንለጎን ወደ ፓርኩ የገቡ ባለ ሀብቶች እንዳሉና አንድ ባለ ሀብት ሰባት ኢንዱስትሪዎችን ይዞ ገብቷል ብለዋል፡፡ የአካባቢው የአየር ሁኔታ ተስማሚ፣ በመሆኑ ባለ ሀብቶች ምርታቸዉን በስኬት ለገበያ ለማቅረብ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡ ለባለ ሀብቶች ለማምረቻ ብቻ 142 ሄክታር የተዘጋጀ መሬት መኖሩንም ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ የኀይል አቅርቦት ግንባታው መዘግየቱን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው “የኀይል አቅርቦትን ለማሟላት የመስመር ግንባታ የተገነባ ቢሆንም ከሰብስቴሽን ወደ ፓርኩ የሚመጣው ዋና ኃይል አልተገነባም፡፡ አሁን ግን የፌድራሉ መንግሥት የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገ በመሆኑ ችግሩ በአጭር ጊዜ ሊፈታ እንደሚችል እምነት አለን” ብለዋል፡፡
የገጠር ሽግግር ማዕከላትን ጨምሮ እስከ አሁን ለፓርኩ ግንባታ 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበትና ግንባታዎቹ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች የተገነቡ እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልጸዋል፡፡ የግብርና ምርት ግብዓቶች በስፋት እንዲቀርቡ ከተለመደው አሠራር በመውጣት የግብርና ግብዓትን ማሻሻል፣ የመስኖ ልማትን ማጠናከርና አርሶ አደሮች ፓርኩን ታሳቢ በማድረግ እንዲሠሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የግብርና ምርትን ለማሳደግ ከየተቋማት የተዋቀረው ግብረኃይል ኮርፖሬሽኑ ጋር በጋራ እንደሚሠሩ ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስገንዝበዋል፡፡
በፓርኩ አማካኝነት 25 ሺህ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል እንደሚፈጠርላቸው ያስረዱት አቶ ደሴ በፓርኩ አማካኝነት በአካባቢው የሚኖረው መስተጋብር በርካታ የሥራ እድልን ሊፈጥር ይችላል፣ የአካባቢውን የግብርና ሥራ በማዘመን ወደ ኢንዱስትሪው ለሚደረገው ሽግግር የጎላ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ በአካባቢው የተገነቡት ሰባት የገጠር ሽግግር ማዕከለታት በዋነኝነት አርሶ አደሮችንና ኢንዱስትሪዉን የሚያገናኙ መሆናቸውን አቶ ደሴ በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል፡፡ ከፓርኩ ምረቃ በኋላ የሀገር ውስጥና የውጪ ባለ ሀብቶች ወደ ፓርኩ ገብተው በሠፊው ማልማት እንደሚጀምሩም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የሕዝቦችን አንድነት የሸረሸረውን የህወሃት የተሳሳተ ትርክት ለማጽዳት እየተሰራ ነው” የክልል ምክር ቤቶች
Next article“እንዲህ ብዙ ሆናችሁ እንደአንድ ስትታዩ ታምራላችሁ” ዶክተር ሂሩት ካሳው