
የሴቶችን ውሳኔ ሰጭነት እና አመራርነት ሚና ማሳደግ የሁሉም ድርሻ መሆኑን ሴት የሥራ ኀላፊዎች ገልጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 25/2013 ዓ.ም (አብመድ) እንደ አማራ ክልል ሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ መረጃ ሴቶች በትውልድ ቀረጻ እና በማኅበረሰብ ግንባታ ረገድ የሚጫወቱት ሚና የላቀ ቢሆንም በአመራርነት እና በውሳኔ ሰጪነት ላይ ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው፡፡ በዚህም በአማራ ክልል በክልል ደረጃ በአመራርነት ላይ የሴቶች ተሳትፎ 19 በመቶ ብቻ ነው፡፡ በችግሮቹ እና በመፍትሔ ሀሳቦች ዙሪያ አብመድ በሥራ ኀላፊነት ላይ ያሉ ሴቶችን አነጋሯል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ አስታጠቅ ግዛው እንዳሉት ሴቶችን በአመራርነት እና ውሳኔ ሰጭነት ለማሳተፍ ጅምር ሥራዎች ቢኖሩም በሚፈለገው ልክ አይደለም፡፡ ሴቶች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፍ የነቃ ተሳታፎ እንዲኖራቸው መዋቅርን መሰረት ተደርጎ ምልመላ እየተካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ አስታጠቅ እንዳሉት በየደረጃው ያሉ አመራሮች “ሴቶች ተቋም ይመራሉ፤ ሕዝብ ያስተዳድራሉ፤” የሚለውን አመለካከት ሙሉ በሙሉ አምነው እንዲቀበሉ ለማድረግ ሴቶች ራሳቸው መታገል አለባቸው፡፡
የሴቶችን ውሳኔ ሰጭነት እና አመራርነት ተሳትፎ በሚጠበቀው ልክ ለማሳደግ ማኅበረሰቡ በሴቶች ላይ የሚደርስን ተጽዕኖ በማስቀረት በኩል የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡ ሴቶች እርስ በርስ ምክክር ማድረግ እና መደጋገፍ እንደሚጠበቅባቸውም መምሪያ ኀላፊዋ ጠቁመዋል፡፡
የደሴ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ ፈንታዬ ጋሻው በአመራርነት እና ውሳኔ ሰጪነት መደቦች የሚመጥኑ ሴቶችን ወደፊት አምጥተው ከማሰራት ይልቅ በደፈናው “የሉም” የሚል ምክንያት እንደሚቀርብ ተናግረዋል፡፡ ሴቶች ሰርተው የላቀ ውጤት ሲያስመዘግቡ እውቅና የሚሰጥበት ሁኔታም ዝቅተኛ በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡ ሴቶች የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽሕፈት ቤትን ለመምራት ብቻ የተፈጠሩ አድርጎ ማየትም እየተለመደ መምጣቱን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ኀላፊዋ ገለጻ የሚሰጣቸውን ኀላፊነት በአግባቡ የሚወጡ ሴቶች ቢኖሩም ወደ ኀላፊነት የሚመጡበት መንገድ ግን በእሾህ የታጠረ ነው፡፡ ወደ አመራርነት እንዲመጡ ሲጠየቁ ያለውን ጫና በመፍራት የሚያፈገፍጉ ሴቶችም መኖራቸውን የመምሪያ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡
ሌላው በአመራርነት ቦታ ላይ በተቀመጡ ሴቶች የሚፈጸመው ደባ ሴቶች ወደ አመራርነትና ውሳኔ ሰጭነት ቦታ እንዳይመጡ ጫና ይፈጥራል፡፡ በኃላፊነት በተቀመጡበት ቦታ ያሉ ሥራዎችን በውጤታማነት በመፈጸም የሚገጥማቸውን ፈተናም በጽናት መወጣት እንደሚገባ አሳስበዋል ወይዘሮ ፈንታዬ፡፡ ሌሎች ሴቶችም በውሳኔ ሰጭነት ቦታው ላይ የተቀመጠችውን ሴት መደገፍ አለባቸው ብለዋል፡፡ የሴቶች ውሳኔ ሰጭነት እና አመራርነት ሚና ማደግ ለኅብረተሰቡ ብሎም ለሀገር ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ ሁሉም ዓላማውን መደገፍ እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ ሴቶች በአመራርነት ቦታ ላይ ሲቀመጡ ለሀገር ግንባታ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ “የሴቶችን የአመራርነት ተሳትፎ አለማሳደግ ሀገራችንን በድህነት ውስጥ እንድትኖር መፍቀድ ነው” ብለዋል ኀላፊዋ፡፡ ሴቶች ያላቸውን እውቀት እንዲጠቀሙበት በሚመጥናቸው ቦታ እንዲቀመጡ አለማድረግ፣ አቅማቸው የጎለበቱ ሴቶች ለሌሎች ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ሁኔታዎችን አለማመቻቸት እና በወንዶች ጫና ስር የወደቁ ሴቶችን አለመደገፍ ሴቶች በአመራርነትና በውሳኔ ሰጪነት ቦታ ላይ በልበ ሙሉነት እንዳይቀመጡ እንቅፋቶች ናቸው ብለዋል፡፡
ማኅበረሰቡም ለሴቶች የሰጠውን የተሳሳተ ግምት ትቶ ሴቶች ትዳራቸውን ሲመሩ ቤተሰብ ሲያስተዳድሩ የሚያውቁትን ኀላፊነት በአግባቡ የመወጣት ልምድ ተግባራዊ እንዲያደርጉት ማገዝ አለበት ብለዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ስልጠና ውይይትና መደጋገፍ አስፈላጊ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ የቢሮ ኃላፊዋ በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ ሴቶችን ቁጥር ከፍ ለማድረግ የመመልመልና የማሰልጠን ሥራ እንየሠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ